Saturday, October 24, 2015

የመንግስት የውጭ ብድር፤ 19 ቢሊዮን ዶላር (390 ቢ. ብር) ደርሷል


Written by  ዮሃንስ ሰ.

• በ2002 ዓ.ም፣ የውጭ ብድር፣ 5.6 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነበር።
• አሁን፣ የውጭ ብድር፡ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሯል - 19 ቢሊዮን ዶላር።
• በ2002 ዓ.ም፣ ለውጭ እዳ 111 ሚ.ዶ ተከፍሏል (ባሁኑ ምንዛሬ 2.3ቢ. ብር)።
• አምና፣ የውጭ እዳ ክፍያው 970 ሚ.ዶ ነበር (ከ14 ቢ. ብር በላይ)።
• በ2002 ዓ.ም፣ የዓመት ወለድ 42 ሚ.ዶ ነበር (ባሁኑ ምንዛሬ ከ1ቢ. ብር በታች)።
• አምና፣ የዓመት ወለድ 250 ሚ.ዶ ተከፍሏል (ከ5 ቢ. ብር በላይ)።

የመንግስት የውጭ ብድር፣ 19 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሰሞኑን ያወጣው አዲስ ሪፖርት ገልጿል። አብዛኛው ብድር፣ ለባቡር ትራንስፖርት፣ ለቴሌ እና ለመንገድ ግንባታ የሚውል ቢሆንም፤ የብድር መጠኑ በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ ነው በማለት የአለም ባንክና የአይኤምኤፍ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት፣ የውጭ ብድር ለመመለስ፣ አገሪቱ 111 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ ከፍላለች። አምና ግን፣ የብድር ወለድ ብቻ፣ ሩብ ቢሊዮን ዶላር (250 ሚ.ዶ) ደርሷል። ወለዱን ጨምሮ፣ ለእዳ ክፍያ የዋለው የውጭ ምንዛሬ ደግሞ፣ 970 ሚ.ዶ ነው ይላል የገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት።
የመንግስት ብድር እና የእዳ ክፍያው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ ከሁለት እጥፍ በላይ የጨመረው፣ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች የሚመጣ ብድር በመብዛቱ እንደሆነ አይኤምኤፍ ገልጿል።
በእርግጥ፣ ካሁን በፊትም፣ በተለይ እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ፣ እንደ በርካታ የአፍሪካ አገራት፣ ኢትዮጵያም ከፍተኛ የብድር እዳ ተከማችቶባት እንደነበር ይጠቅሳል አይኤምኤፍ። በዓመት፣ ከኤክስፖርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ብቻ በነበረበት በዚያ ወቅት፣ የአገሪቱ የብድር እዳ ወደ 8 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። አብዛኛው እዳ የተቃለለውም፣ በብድር ስረዛ ነው። በሚሌኒዬሙ መባቻ ላይ የእዳ ክምችቱ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በታች ወርዶ እንደነበር የአይኤምኤፍ መረጃ ያሳያል። ግን እዚያው አልቆየም።
ከነባሮቹ አበዳሪዎች በተጨማሪ፣ ለቴሌኮሙኒኬሽን ማስፋፊያ ከቻይና የመጣ ብድር እንዲሁም፣ ለመጀመሪያዎቹ የስኳር ፕሮጀክቶች የህንድ ብድር ታክሎበት፣ በ2002 ዓ.ም የመንግስት የእዳ ክምችት፣ ወደ 5.6 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። ከዚያ ወዲህ፣ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አማካኝነት የተጀመሩት በርካታ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ደግሞ፣ የመንግስትን እዳ በሁለት እጥፍ እንዲጨምር አድርገዋል - በተለይም ከአዳዲስ አበዳሪዎች።
ከትልቁ ነባር አበዳሪ፣ ከአለም ባንክ የሚመጣ ብድር ቀንሷል ማለት አይደለም። ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የነበረው የባንኩ የብድር ክምችት፣ አምና 4.5 ቢ. ዶላር ደርሷል። የአፍሪካ ልማት ባንክና ፈንድ ሲጨመርበት ስድስት ተኩል ቢሊዮን ዶላር ሆኗል - የብድር ክምችቱ። እነዚህ ነባር አበዳሪዎች ናቸው።
ግን አዳዲሶቹ አበዳሪዎችም አሉ - በተለይ ቻይና። የቻይና ብድር፣ ሁለት ዓይነት ነው። በቀጥታ የሚመጣ ብድር አለ - ለምሳሌ ለባቡር መስመር ግንባታ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በዜድቲኢና በሁዋዌ አማካኝነት፣ ለቴሌኮም ማስፋፋፊ የሚመጣ ብድር አለ። ሌሎቹ አዳዲስ አበዳሪዎች፣ ህንድ (ለምሳሌ ለስኳር ፕሮጀክቶች)፣ እንዲሁም ቱርክ (ለባቡር መስመር ዝርጋታ) ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ አገራት የመጣ የብድር ክምችት፣ በ2002 ዓ.ም፣  ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በታች ነበር። አምና ግን፣ የእነዚሁ የብድር ክምችት፣ 8.5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ሆኗል።
የነባሮቹና የአዳዲሶቹ ሲደማመር፣ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ራሱን ችሎ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለማስመጣት፣ የሚወስደው ብድር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ቢመጣም፤ አየር መንገዱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኝ ድርጅት ስለሆነ፣ ብዙም አሳሳቢ እንዳልሆነ ይገልፃሉ - አይኤምኤፍና የአለም ባንክ።
ካሁን በፊት ያልነበረና አምና የተጀመረ ሌላ የብድር አይነትም አለ - “የውጭ የቦንድ ብድር”። መንግስት፣ በአስር አመት ብድር እንደሚመልስ ቃል በመግባት (ቦንድ በመሸጥ/ ማለትም ምስክር ወረቀት በማስያዝ)፣ አምና አንድ ቢሊዮን ዶላር ተበድሯል። እንዲህ አይነቱ ብድር፣ “ለዚህኛው” ወይም “ለዚያኛው” ፕሮጀክት ተብሎ የሚመጣ ስላልሆነ፣ ለመንግስት አመቺ ነው። ነገር ግን፣ ወለዱ ከፍተኛ ነው - ከሌሎች ብድሮች ጋር ሲነፃፀር፣ የዚህኛው ወለድ ከሦስት እጥፍ በላይ ነው። የአብዛኞቹ ብድሮች ወለድ፣ በአመት ከ2 በመቶ በታች ነው። የቦንድ ብድሩ ወለድ ግን፣ 6.6 በመቶ።
መንግስት፣ ዘንድሮ 1 ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ብድር ለመጨመር፣ ድርድር እንደጀመረ ተገልጿል።
ይህንን ነው፣ “በጣም አሳሳቢ” ብለው የሚፈርጁት - የአለም ባንክና አይኤምኤፍ። አንደኛ ነገር፣ ከጥቂት ዓመታት ውስጥ፣ የውጭ እዳው በፍጥነት እየተገዘፈ መምጣቱ አሳሳቢ እንደሆነ ይገልፃሉ። ሁለተኛ ነገር፣ የብድሩ ዓይነት፣ ለከፍተኛ የወለድ ክፍያ የሚዳርግ መሆኑ ደግሞ፣ ተጨማሪ ስጋት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።
ከ2002 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር፣ መንግስት ለእዳ ክፍያ የሚያውለው የውጭ ምንዛሬ፣ ከ111 ሚ.ዶ ወደ 970 ሚ.ዶ ከፍ ብሏል። ከዚሁ ውስጥ፣ የወለዱ መጠን ስንት እንደሆነም ይታወቃል። በ2002 ዓ.ም፣ የወለዱ መጠን 42 ሚ.ዶ ነበር። አምና ደግሞ፣ የወለድ ክፍያው 250 ሚ.ዶ።
የእዳ ክፍያ ከነወለዱ፣ ባለፉት አምስት አመታት፣ ወደ ስምንት እጥፍ ጨምሯል። ይህንን የሚያካክስ፣ የኤክስፖርት ገቢ እየጨመረ ይመጣል ተብሎ ነበር የታሰበው። ነገር ግን፣ ባለፈት አራት ዓመታት፣ ከኤክስፖርት የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ አላደገም። 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ላይ ቆሟል። የእዳ ክፍያን ከነወለዱ ለመሸፈን የሚያስችል የኤክስፖርት እድገት አለመገኘቱ፣ ትልቁ አሳሳቢ የኢኮኖሚ ችግር ነው። እንዲያውም፣ ፈታኝ ቀውስ ያልተፈጠረው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛ፣ በአለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ፣ መንግስት፣ በነዳጅ ግዢ ሳቢያ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ከማፍሰስ ድኗል። ሁለተኛ፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በየአመቱ የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ ጨምሯል።
የውጭ ብድር እንዳለፉት አምስት ዓመታት በፍጥነት እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ግን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እየጎላ መምጣቱ አይቀርም።
በሌላ በኩል፣ እንደውጭ ብድር፣ የመንግስት የአገር ውስጥ ብድርም እየጨመረ እንደመጣ፣ የገንዘብ ሚኔስቴር ሪፖርት ይገልፃል። በ2003 ዓ.ም፣ የብድር ክምችቱ ከ120 ቢሊዮን ብር በታች ነበር። አምና ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ደርሷል። 

No comments:

Post a Comment