Friday, October 23, 2015

“ተመስገንን ማየት አትችሉም!”

ከታሪኩ ደሳለኝ

ወንድማችን ተመስገን ሀሳቡን በነጻነት ስለገለጸ እና ጽሁፎችን በጋዜጣ ስላተመ ብቻ ሶስት ዓመት ተፈርዶበት ወደ ዝዋይ እስር ቤት ከተላከ ዛሬ 374 ቀናት ሆነው፡፡ በተለያየ ጊዜ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ቢደርስበትም ሁሉን ችሎ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ለሚያሰቃየው የወገብ እና የጆሮ ህመም ህክምና ሳያገኝ ዛሬም ህመሙን እየታገለ አለ፡፡ የታሰረበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ይህንን ችግሩን እና የሚደርስበትን እንግልት አስመልከቶ እኛም፣ ወዳጆቹም ለመናገር ሞክረናል፡፡ አቤቱታችንን እና ጩኸታችንን ተከትሎ ችግሮቹ ይስተካከላሉ ብለን ብናስብም ይባስ ብሎ በገደብ የተፈቀደለት የቤተሰብ ጥየቃ እንዳያገኝ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ ተከልክሏል፡፡

ወንደሞቹ ወደ ዝዋይ እስር ቤት ተመላልሰን ያጋጠመንን ከዚህ በታች አንብቡት እና እናንተው ፍረዱ፡፡ አንዴ አይደለም ሁለት፣ ሶስት፣ አራት ጊዜ “አይቻልም” ተብለናል፡፡

ክልከላ 1፡- እሁድ ጥቅምት 7/ 2008 ጠዋት ታላቅ ወንድማችን ዝዋይ ሰደርስ በአዋራና በፀሀይ ተቃጥሎ ነበር፡፡ የዝዋይ እስር ቤት መንገድን የቀመሰ ያውቀዋል፡፡ የእስር ቤቱ መግቢያ በር ላይ የተጠያቂ ስም ሲያስመዘግብ “ተመስገን ደሳለኝ” አለ፡፡
“እሱን መጠየቅ አይቻልም” አለ መዝጋቢው የእስር ቤት ወታደር፡፡
“ለምን?” ጠየቀ ወንድማችን፡፡
“ትላንት ማታ የደረስን ትዕዛዝ ነው”
“ማነው ያለው?”
“ከበላይ ነው”
“ምን ማለት ነው?”
“በማንም እንዳይጠየቅ ማለት ነው፡፡ አሁን ተመለስ” የእስር ቤቱ ወታደር ቆፍጠን ያለ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
“እሺ ምግቡን ላስገባ” ወንድማችን በመጨነቅ ጠየቀ፡፡
“አይቻልም” ቁርጥ ያለ ክልከላ፡፡

ክልከላ 2፡- ሰኞ ጥቅምት 8/2008
ሌላኛው ወንድማችን ወደ ዝዋይ እስር ቤቱ አቅንቶ “የተመስገን ወንድም ነኝ” ሲል ፈጣኝ ምላሽ ተሰጠው፡፡
“የያዝከውን ምግብ ይዘህ ቀኝ ኋላ ዙር” ከጠባቂዎቹ ወታደሮች አንዱ የሰጠው መልስ ነበር፡፡
“በምን ምክንያት?” ወንድማችን ጠየቀ፡፡
“አይመለከትህም!”
“ወንድሜ እኮ ነው!”
“እናውቃለን፡፡ ትዕዛዝ ነው!”
“እሺ ምግቡን እንኳን ላስገባ”
“አይቻልም፡፡ ውጣ!”

ክልከላ እና ፍቃድ መሳይ 3፡- ማክሰኞ ጥቅምት 9/2008
ከአዲስ አበባ በጠዋት ተነስቼ ረፋድ ላይ ዝዋይ እስር ቤት ደረስኩ፡፡
“ተመስገን ጋር ነው የምገባው” አልኩኝ ለተረኛ መዝጋቢ ወታደር፡፡
“ምኑ ነህ?”
“ወንድሙ”
“ግባ” አላምንኩም!
የያዝኩትን ምግብ አስፈትሼ ከሩጫ በማይተናነስ እርምጃ ተመስገን ወደሚጠየቅበት ታዛ ፈጠንኩ፡፡ ለወታደሮቹ እንዲጠሩልኝ ስሙን ሰጥቼ ተቀመጥኩኝ፡፡ ተሜ ሳይመጣ 40 ደቂቃ አለፈ፡፡ አንድ ወታደር በብስክሌት መጥቶ “ተነስና ውጣ፡፡ በስህተት ነው የገባኸው” አለኝ፡፡
ከተሜ በሜትሮች ርቀት ያህል ርቀት ተቀምጩ ሳላየው መውጣቴ ቢያስጨንቀኝም እኔም እንደወንድሞቼ ከመጠየቅ ወደኋላ አላልኩም፡፡
“ማነው አይጠየቅም ያለው?”
“ትዕዛዝ ነው” ባለፉት ሁለት ቀናት ስንሰማው የነበረው ተመሳሳይ መልስ ተሰጠኝ፡፡
“እሺ የያዝኩትን ምግብ ላቀብለው”
“አትሰጠውም”
“እሺ ከኃላፊ ካለ አገናኘኝ” አልኩት ወታደሩን
ወታደሩ አጠገቡ ካለው ወታደር ጋር በአይኑ ተነጋግሮ በምልክት ቢሮውን አሳየኝ፡፡ የያዝኩትን ስንቅ አስቀምጩ “አስተዳዳር” የሚል ጽሁፍ በሩ ላይ ከተለጠፈበት ክፍል አንኳኩቼ ስገባ ሰባት በኃላፊነት ደረጃ ላይ እንዳሉ ማዕረጎቻቸው የሚያሳብቁ ወታደሮች ተሰባስበው አገኘኋቸው፡፡
የሰብሳቢ ወንበር ላይ ፈንጠር ብሎ የተቀመጠው ወታደር “ምንድነው?” አለኝ
“ወንድሜን አትጠይቅም ተብዬ ነው” መለስኩ፡፡
“ማነው ስሙ?”
“ተመስገን ደሳለኝ”
የተማከሩ በሚመስል ሁኔታ አንድ ላይ “እሱን መጠየቅ አይቻልም” አሉኝ፡፡
“ለምን?”
ሰብሳቢው ወታደር “አያገባህም” ብሎኝ አጠገቡ ያለውን መገናኛ ሬድዬ አንስቶ “የጋዜጠኛ ተመስገን ወንድም ነኝ ባይ እንዴት እዚህ ድረስ መጣ” ሲል ጠየቀ፡፡
የሬድዮን መልስ ልሰማ ስል “ውጣ እና በር ላይ ጠብቀኝ” አለ
ወጣሁ፡፡ እኔ ከወጣሁ ከ15 ደቂቃ በኋላ ሁለት ሬድዮ የያዙ ወታደሮች መጥተው ወደ መጠየቂያው ቦታ በድጋሚ ወሰዱኝ፡፡ ስደርስ ተሜ በስድስት ወታደሮች ተከቦ አገኘሁት፡፡ እኔን ካመጡኝ ወታደሮች ጋር ሲደመሩ ስምንት ሆኑ ማለት ነው፡፡ ከተሜ ጋር ሰላምታ ተለዋውጠን ማውራት ጀመርን፡፡
“ማዘር ምን ሆና ነው ያልመጣችሁት?” ጠየቀ ተሜ፡፡
“ኧረ! ምንም አልሆነችም፡፡ ከእሁድ ጀምሮ አትገቡም ብለውን ነው” አልኩት፡፡
ተሜ ወታደሮቹን እየተመለከተ “ለምንድነው የተከለከልኩት?” አለ፡፡
ሬድዮ የያዘው ወታደር ወደ እኔ እየተመለከተ “አሁን እሱን አናግረው” አለው፡፡
“ጉዳዩ ከእሱ ጋር አያይዝም” ተሜ መለሰ፡፡
ወታደሩ ወዲያውኑ “ተነስ” አለኝ
“ወዴት?” አልኩት
ተሜ ጣልቃ ገብቶ “ጉዳያችሁ ከእኔ ጋር መሰለኝ” አላቸው፡፡
መልስ አልመለሱትም፡፡ አንደኛው ወታደር ወደ እኔ ዞሮ “አንተ ሂድ” አለኝ፡፡
ሶስተ ደቂቃ በማይሞላ መተያየት ከሰላምታ የዘለለ ነገር እንኳ ሳናወራ ለመውጣት ተነሳሁ፡፡ የተሜን አይን አይን እያየሁ ሰወጣ ተሜ ስምንት ወታደሮች እንደከበቡት እያወራ ነበር፡፡ ምን እንደሚል መስማት አልቻልኩም፡፡ ከእስር ቤቱ ወጣሁ፡፡

ክልከላ 4፡- ሐሙስ ጥቅምት 11/ 2008
ሰኞ ዕለት ተሜን ሳያይ እንዲመለስ የተደረገው ወንድማችን ዝዋይ እስር ቤት ሲደርስ ገና ከበር “ተመስገንን መጠየቅ አይቻልም” አሉት፡፡
“ማክሰኞ ወንድሜ ገብቶ ነበር”
“አልገባም፡፡ ገብቶም ከሆነ በስህተት ነው”
የሚለው ሲያጣ “እሺ ያመጣሁትን ስንቅ ላቀብለው”
“አይቻልም ተመለስ”

ከሰኞ እስከ ሐሙስ በተደጋጋሚ ተሜን ለማየት እና ስንቅ ለማቀበል ያደረግነው ሙከራ እንግዲህ ይህን ይመስላል፡፡ “ይህ ተመስገናችሁ የእኛ እስረኛ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ህክምና እንደከለከልነው፣ መርጠን በሰው እንዳስጠየቅነው፤ ዛሬ ደግሞ ማንም እንዳይጎበኘው ማድረግ መብታችን ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ማንም እሱን መጠየቅ አይችልም” ብለዋል የዝዋይ እስር ቤት ሹሞች፡፡

ተሜ ህገመንግስታዊ መብቱ ተገፍፎ፣ ሰብዓዊ መብቱ ተጥሶ እና በህመም እየተሰቃየ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው?

The post “ተመስገንን ማየት አትችሉም!” appeared first on Zehabesha Amharic.

Source:: Zehabesha

No comments:

Post a Comment