Wednesday, September 2, 2015

በግለሰቦች እጅ የሚገኘውን የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መልሶ ለመቀማት እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡


ነኅሴ ፳፯ (ሀያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአማራ ክልል ከምርጫ 2007 በፊት ህብረተሰቡ መሳሪያ እንዲታጠቅ በመፍቀድ ህጋዊ ያደረገውን የመሳሪያ ፈቃድ በመንጠቅ መሳሪያዎችን ለመሰብሰብ ስልቶችን እየቀየሰ መሆኑ ምንጮች ለኢሳት አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት ህገወጥ የጦር መሳሪያ ህጋዊ ለማድረግ ምዝገባ ካካሄደ በኋላ የመሳሪያ ፍቃድ በመስጠት ህብረተሰቡ ራሱን እንዲከላከልበት መፍቀዱን ተከትሎ፣ ከአጎራባች ክልሎች በተለይም ከትግራይ ክልል በተሰማው ተቃውሞ በየግለሰቡ እጅ ያለውን ነፍስ ወከፍ መሳሪያ ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል፡፡
ሰሞኑን ግልጽ ባልሆነና አብዛኛው የህብረተሰቡ ክፍል ሊያየው በማይችል ሁኔታ አጫጭር ማስታወቂያዎችን በክፍለ ከተማ ደረጃ በማውጣት ከአሁን በፊት ጊዜያዊ የመሳሪያ ፈቃድ የወሰዱ ሁሉ በየሚኖሩበት አካባቢ በመገኘት ለህዝብ እንዲያስተቹና የህዝቡን ይሁንታ ካገኙ ቋሚ ፈቃድ ለመስጠት በተጠቀሰው ጊዜ የማይገኝ መሳሪያውን ገቢ ለማድረግ የሚያስችለውን አካሄድ መጀመሩ ታወቋል፡፡
የስብሰባው ጥሪ ማስታወቂያ የታጠቁ አካላት በህዝብ ይተቻሉ ቢልም በተጠቀሰው ቀን ህብረተሰቡ ተገኝቶ እንዲተቸ የተደረገ ጥሪ አለመኖሩ በገዢው መንግስት የታሰበ ተንኮል እንዳለ ጠቋሚ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ፡፡
ከአሁን በፊት ህጋዊ ሆነዋል በማለት ከእያንዳንዱ ባለመሳሪያ ከሁለት መቶ ሃምሳ ብር በላይ በመሰብሰብ መታወቂያ መስጠቱ እየታወቀ በአጭር ጊዜ ቀርባችሁ በህዝብ ካልተተቻችሁ መሳሪያውን እንነጥቃለን የሚል መንፈስ ባለው ማስታወቂያ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ መጠራታቸው አግባብ አንዳልሆነ ታጣቂዎች ይናገራሉ።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት በልዩ ልዩ ክፍለ ከተሞች ምዝገባውን ለማካሄድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ሙከራ ቢያደርግም ምንም አይነት ታጣቂ ቀርቦ አለማስመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹ የመሳሪያ ፈቃዱ በየአካባቢው አመራሮች በወቅቱ ተተችቶ እንድንይዝ ተፈቅዶልናል፡፡ ›› የሚሉት መሳሪያ ታጣቂዎች ፣ ‹‹ በወቅቱ በአመራሮች ስንገመገም መያዝ አይፈቀድላችሁም ብንባል ለመሳሪያ ግዢ ያወጣነውን ከሐምሳ ሽህ ብር በላይ አንከስርም ነበር፡፡ ›› በማለት አሁን የገዢው መንግስት ሊሰራ ያሰበው ሴራ ደም መፋሰስን ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራሉ፡፡
በአብዛኛው የሰሜን ጎንደር የሚገኙ ታጣቂዎች ለአንድ ክላሽንኮቭ መሳሪያ እስከ ስልሳ ሽህ ብር በማውጣት ገዝተው ለራሳቸውና ለንብረታቸው መጠበቂያ ቢያስፈቅዱም፣ አሁን በተጀመረው መሳሪያዎቹን የመንጠቅ እንቅስቃሴ በመቃወም ትጥቅ አንፈታም በማለት ከገዢው መንግስት አመራሮች ጋር መፋጠጣቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡
በኢህአዴግ ግምገማ ወቅት የህወሃት ጻሃፊ፣ የክልሉ መሪ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አማራውን እያስታጠቀ፣ ራሱን ጄኔራል አድርጎ ሾሟል በማለት መገምገማቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። ሁለቱ ክልሎች በአጎራባች ወረዳዎች የይገባኛል ጥያቄ እየተወዛገቡ ነው። የትግራይ ክልል አማራ ክልል ህጋዊ የጦር መሳሪያ ፈቃድ መስጠቱን አጥብቆ ተቃውሞ ነበር። አሁን በህዝብ ግምገማ ስም መሳሪያ ለመቀማት የተላለፈው መመሪያም ከዚሁ ተቃውሞ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

No comments:

Post a Comment