Wednesday, November 4, 2015

ብሄራዊ መግባባትና መልካም አስተዳደር “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” መሆን የለበትም!! – ሸንጎ


ጥቅምት 22፣ 2008 (ኖቨምበር 2፣ 2015)

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን አስከፊ ሁኔታ ቀይሮ አንድነቷ በተጠበቀ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሰው ከፍራቻና፣ከሰቆቃ ተላቆ መብቱ ተረጋግጦ ፣ እንዲኖር እነሆ ትግሉን ከጀመረ ውሎ አድሯል።

ይህን ራእይ ተግባራዊ ለማድረግም ህዝብን ያማከለ፣ ሰላማዊ፣ ትግል የማካሄድ፣ አስፈላጊነትን አምኖ ይሀንኑም በራእይ ደረጃ አስቀምጧል። ከዚህም አልፎ ታቃዋሚው በሀገር ቤት ወይም በውጭ ሀገር የሚገኝ በሚል አላስፈልጊ ክፍፍል ወይም መሰረታዊ ባልሆኑ የልዩነት ነጥቦች ላይ በማተኮር ራሱን እና አጠቃላይ ትግሉን ከሚጎዳ አካሄድ ተቆጥቦ፣በጋራ ለመቆም የሚያሰችለው የትግል አንድነት እንዲፈጥርና አቅሙንም እንዲገነባ ደግመን ደጋግመን አሳስበናል።
አሁን ባለው ሁኔታ ሽንጎ ትልቁ የአንድነት ሀይሎች ስብስብ ቢሆንም አሁንም ገና ወደአንድ ጎራ ሊሰባሰቡ የሚገባቸው እጅግ ብዙ ድርጅቶች፣ስብሰቦችና ግለሰቦች እንዳሉ ግልጽ ነው። ይህን ሃይል አሰባስቦ አይበገሬ ያንድንት ሀይል መፍጠርና ትግሉን ማፋፋም፣ እያደር ወደተወሳሰብ ጎዳና በማምራት ላይ የምትገኘውን ሀገራችንንና ህዝባችንን ለመታደግ ዋነኛው መሳሪያ ነው። ይህ መሰረታዊ ዋሰትና ሳይዘገይ ተግባራዊ እንዲሆንም አሁንም ሳንታክት ጥረታችንን እንቀጥላለን።
የትግላችን ራእይ የግፍ እና የኣድልኦ ስርአት አክትሞ፣ የህግ የበላይነት፣ ሰብአዊ መብት፣ የሁሉም ዜጋ የግልና የጋራ መብት የሚከበርበት በሁሉም ባለድርሻዎች ሙሉ ተሳትፎ የዳበረ ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲአዊ ስርአትን እውን ማድረግ ነው።

ሽንጎ ደግሞ ደጋግሞ እንደገለጸው እና ባለፈው ነሀሴ ባካሄደው ጉባኤው እንዳጸደቀውም፣ የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት፣ የሁሉንም ዜጎች አወንታና ታአማኒነትን ያገኘ ስርአት ለመመስረት ሀገራችን ያላት አማራጭ በብሄራዊ መግባባትና በብሄራዊ እርቅ ጎዳና መጓዝ ነው።
ይህ ሂደት ካግላይነት የተላቀቀ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳተፈ፣ የሁሉንም ድምጽ ለማዳመጥ፣ የቆረጠ፤ ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትሄን ለመፈለግ የሚያስችል መሆን ይገባዋል። በኛ አመለካከት ብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ የተወሰኑ ክፍሎች ወይም ድርጅቶች ከደረሰባቸው ውጥረት ለመወጣት የሚጠቀሙበት የጊዜ መግዣ ታክቲክ ሳይሆን በሀገራችን ውስጥ የሚታዩ ፖለቲካዊ፣ማሀበራዊና ሌሎችንም ችግሮቻችንን ፊት ለፊት በጋራ መርምረን በአርቆ አሳቢነት፣ በብሰለትና፣ በመቻቻል፣ በወንድማዊና እህትማማች ስሜት፣ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረግ እውነተኛ ጉዞ ነው መሆን ያለበት።

ይህ ሲሆን ብቻ ነው ለዘላቂ ሰላም፣ ለልማት፣ ለምንመኛት ታላቅ የበለጸገች ኢትዮጵያ መሰረት የምንጥለው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው፣ አላስፈልጊ ደም መፋሰስን፣ የእርስ በርስ መጠፋፋትን ፣ የንብረት መውደምን፣ ስደትን፣ ጽንፈኛነትን፣ ቂም በቀልን አስወግደን ከራሷ ጋር የታረቀች ፣ የጦርነት አዙሪትን የሰበረች ከውጭ ሊሰነዘር ለሚችል ጥቃት ያልተጋለጠች ፖለቲከኞች ከስልጣን በተወገዱ ቁጥር፣ለእስር ወይም ለስደት የማይዳረጉባት ንብረታቸው ከሀግ ውጭ የማይነጠቅባት፣ሀገርና፣የፖለተካ ስርአትን ለመመስረት የሚያሰችል መሰረት የምንጥለው።

በዚህ አንጻር ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የገዥው ህወሀት/ኢህአዴግ መሪ ጠቅላይ ሚኒሰተር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ መንግስታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የነጻ ፕሬስን መብት ለማክበርና ከተቃዋሚዎች ጋር በሀገሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ፍላጎት እንዳለቸው ፣ሌሎችም በህጋዊነት እንዲንቀሳቀሱ ሲሉ ተናግረዋል።
በሸንጎው አመለካከት አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የችግሩ አንዱ አካልና ዋናው መሠረት በመሆኑ የሀገራችንን የተወሳሰበ ሁኔታ ለብቻው ሊቀይረው ከቶውንም አይችልም፡፡ እንዲያውም አሁን ባለው መልኩ እየቆየ በሄደ ቁጥር የሚወስዳቸው እርምጃወች ችግሩን ወደባሰ መወሳሰብ ያሳድገዋል። በሀገራችን ውስጥ ጎልተው ከሚታዩት ብሶቶችና ጥያቄዎች አንጻር ሲታይ አንድ ድርጅት በተናጠል ልዩ መፍትሄ አምጥቶ ሁሉንም ሊያረካ አይችልም።ይህ ቢሆን ኖሮ የህወሀት/የኢህአዴግ የ24 አመታት ጉዞ የኢትዮጵያን ችግር በፈታው ነበር።

የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች በትክክል መረዳት እና መቅረፍ የሚቻለው ለጥቂት ሰአታት በጠባብ አጀንዳ ላይ ለተቃዋሚዎች ገለጻ በመስጠትና በገዥው ቡድን እቅድ ላይ “ሀሳባችሁን አካፍሉን “ ወይም “ወደሀገር ተመልሳችሁ ስሩ” ከሚል ንግግር ባሻገር ሁሉንም አሳታፊና እውነተኛ በሆነ ብሄራዊ መግባባትን እውን ሊያደርግ በሚችል ሂደት ነው።

በሀገራችን ውስጥ የሚታየውን አይነት የተወሳሰበ ችግር መፍታት የሚቻለው አንዱ መፍትሄ ሰጭ ሌላው ደግሞ መፍትሄ ተቀባይ በሚሆኑበት አካሄድ ሳይሆን ሁሉም የችግሮቹ ባለቤት ሁሉም ደግሞ የመፍትሄዎቹም ባለቤት ሲሆኑ ነው። የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች መፍታት የሚቻለው ፍትህን፣ መተማመንና፣ አርቆ አሳቢነትን መሰረት አድርጎ ያለፉ ችግሮች እንደገና እንዳይደገሙ ምን መደረግ እንዳለበት ዋና ዋና በሆኑ ጉዳዮች ላይ በግልጽ ተነጋግሮ መግባባትና መስማማት ላይ መድረስ ሲቻል ነው።

ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦታ ሊኖራት ይገባል፤ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያው ቅሬታ፣ የሚደመጥባት፣ መፍትሄም የሚፈለጋባት ልትሆን ይገባል። ኢትዮጰያ በዜጎቿ መካከል የበኩር ልጅ እና የእንጀራ ልጅ የሚባለው አይነት አድልኦ ለማስተናገድ የማትመች መሆን አለባት።ኢትዮጵያ አንዱ ሌላውን “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ፣ ከቻላችሁ ሞክሩን” የሚባልባት ሀገር መሆን የለባትም።

ይህን እውን ለማድረግም ማንንም ያላገለለ ሁሉም ባለድርሻዎች በሚሳተፉበት የብሄራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ ሂደትን እውን ማድረግ ይጠይቃል።ይህ ሂደት ድፍረትን የሚጠይቅ ነው። ሀገሪቱንና ህዝቧን አሁን ወደሚገኙበት ውስብስብ ሁኔታ ካደረሳቸው አካሄድ መላቀቅን የግድ ይላል። ይህ ሂደት በዜጎች መካከል ፣ በተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል፣ ወዘተ እምነትን መገንባትን እና እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ ያሁኑ “ጥሪም” የፖለቲካ ጊዜ መግዣ አለመሆኑን ማረጋገጥን ይጠይቃል። ይህን ሁኔታ የሚጠይቀውን የመተማመን መሰረት ለማጣል ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁትን የፖለቲካ እስረኞች ጋዜጠኞች ወዘተ መፍታት ለነጻ ፕሬሱና አሁን በህጋዊነት ተመዝግበው በመስራት ላይ ለሚገኙት የፖለቲካ ድርጅቶች ደግሞ የመፈናፈኛ ሜዳውን ማመቻቸት አንድ ታላቅ እርምጃ ይሆናል።

ይህ ባልሆነበት “ኑ ተሳተፉ; ምክክር እናድርግ” ማለቱ “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” በሚለው በሀገራችን ብሂል የሚገለጥ ይሆናል።ይህ ደግሞ የሀገራችንን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ይበልጥ ያባብሰዋል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

The post ብሄራዊ መግባባትና መልካም አስተዳደር “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” መሆን የለበትም!! – ሸንጎ appeared first on Zehabesha Amharic.

Source:: Zehabesha

No comments:

Post a Comment