Thursday, January 19, 2017

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋራ መኖርያ ቤቶችን በተመለከተ “የተሳሳተ” መረጃ አቅርበዋል


ዋዜማ ራዲዮ- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥታቸውን ሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በዚሁ ማብራሪያቸው በሕዝብ እንደራሴዎች ከተነሱላቸው ጥያቄዎች አንዱ የጋራ መኖርያ ቤት ግንባታን የተመለከተ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ የጋራ መኖርያ ቤቶች ‹‹ግንባታ ቆሟል›› የሚባል ወሬ እንዳለና የቤቶች ግንባታ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባታ ቆሟል የሚለውን ወሬ ማስተባበላቸው ይታወሳል፡፡
“ከብድር አቅርቦት መዘግየትና ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ” የተወሰነ መቀዛቀዝ እንደነበር ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ዓመት 131ሺ ቤቶች ግንባታ ላይ እንደሚገኙ፣ ከነዚህ ዉስጥ 30ሺ የሚኾኑት በያዝነው ዓመት መጨረሻ ለነዋሪዎች እንደሚተላለፉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ኾኖም ዋዜማ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት አስተዳደር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ባገኘችው መረጃ በዚህ ዓመትም ኾነ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ነዋሪዎች የሚተላለፍ አንድም የጋራ መኖርያ ቤት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይህ ግን የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶችን አያካትትም፡፡
እንደ ጽሕፈት ቤቱ ገለጻ መንግሥት ከገጠመው የገንዘብ ቀውስ ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት አንድም አዲስ የቤት ፕሮጀክት እንዳይጀመር መመሪያ የተላለፈው ከወራት በፊት ነው፡፡ ‹‹እስከዚያው እጃችን ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን እንጨርስ በሚል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነበር›› የሚሉት የጽሕፈት ቤቱ ባልደረባ ኾኖም አሁን ግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችን ራሱ ለማስፈጸም የሚያስችል የገንዘብ አቅም እንደሌለ ተረድተናል ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ እንደራሴዎች በዚህ ዓመት መጨረሻ 30ሺ ቤቶች ለነዋሪዎች ይተላለፋሉ ማለታቸውን በተመለከተ እንደማንኛውም ሰው ጉዳዩን በሚዲያ እንደሰሙ የገለጹት ይኸው የቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ባልደረባ “በእርግጠኝነት ነው የምነግርሽ ለዚህ ዓመት የሚደርስ አንድም ቤት አይኖርም፤ ቢኾን እኮ እኛም ደስ ይለናል” ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ “ምናልባት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያን ያሉት ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም ሕዝቡ ተስፋ እንዳይቆርጥ” በሚል ሊኾን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡
ቀጣዩ 12ኛ ዙር የጋራ መኖርያ ቤቶች እጣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ካልሆነ መቼ ሊሆን ይችላል ተብለው የተጠየቁት የጽሕፈት ቤቱ ባልደረባ፣ “አሁን ግንባታ ላይ ያሉት የ20/80 ቤቶች ገና በጅምር ላይ ናቸው፣ 35 በመቶ የደረሱት እንኳ ጥቂት ናቸው፣ እንደኔ ግምት በ2010 መጨረሻ ሐምሌ አካባቢ ጥቂት ቤቶች ሊደርሱልን ይችላሉ›› ካሉ በኋላ ‹‹በተጨባጭ እናውራ ካልን በ2011 የመጀመርያ ነባር ተመዝጋቢዎችን ፍላጎት አሟልተን እንጨርሳለን›› ሲሉ ቀጣዩን ዙር በ2 ዓመት ይገፉታል፡፡ ሲያጠቃልሉም “…እንዴትም ቢሠራ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃል መጠበቅ አይቻልም፣” ብለዋል፡፡ የቤቶቹን ብዛት በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት 30ሺ ቤቶች ሳይኾን 26ሺ ቤቶች ብቻ ናቸው ለ12ኛ ዙር በግንባታ ሂደት ላይ ያሉት፡፡ እነዚህም የ20/80 መርሀግብር ቤቶች ናቸው፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ባለሞያ ጨምረው እንደሚሉት ከነዚህ የ20/80 ቤቶች ይልቅ አሁን በጥሩ የግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት የ40/60 ፕሮጀክቶች እንደሆኑና ከእነዚህ ዉስጥ 20ሺህ የሚኾኑት ምናልባት በ2010 መጨረሻ ዕጣ ሊወጣባቸው እንደሚችል የመሥሪያ ቤታቸውን የድርጊት መርሀ ግብር ሰሌዳ አመሳክረው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በንግድ ባንክ በኩል እንዲተላለፉ የተወሰኑ የ40/60 መርሐግብር የመጀመርያ ዙር ዕጣ በየካቲት መጨረሻ አልያም በመጋቢት መጀመርያ ሊወጣ እንደሚችል፣ ዝግጅቱና ሰነድ ርክክቡ ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን እንደሚያውቁ አብራርተዋል፡፡ እነዚህ ቤቶች ግን በቁጥር 1ሺህ 292 ብቻ ናቸው፡፡
መንግሥት ከሕዝብ በሚደርስበት ጫና የተነሳ የቤቶች ግንባታ እንዲፋጠን ከፍተኛ ፍላጎት አለው የሚሉት ባለሞያው ይህን ተከትሎም እኛ ላይ ግፊቱ እየበረታ መጥቷል ይላሉ፡፡ ኾኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹በቂ የገንዘብ አቅርቦት›› እየደረሰን አይደለም፤ ከንግድ ባንክ ጋር በብደር አሰጣጥ ዙርያ አለመግባባቶች አሉ፤ የበጀት እጥረትና ከብረት ግዢ ጋር ተያይዞ ያላግባቡን ነገሮች አሉ ሲሉም የመዘግየቱን ምክንያት ይተነትናሉ፡፡ በአንጻሩ በመሬት አቅርቦት ረገድ ችግር እንደሌለና ኾኖም ከበጀትና ተያያዥ ጉዳዮች የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሂደቱ አዝጋሚ እየሆነ መምጣቱን አልሸሸጉም፡፡
የ40/60 ቤቶች ተቋራጮች ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ከክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ ሥራ ማቆማቸው ይታወሳል፡፡ ኾኖም ባለፈው ወር መጠነኛ ገንዘብ በመለቀቁ አንዳንድ ሳይቶች ላይ ግንባታዎች በከፊል ማንሰራራት ጀምረዋል፡፡ ከዚህ ዓመት መባቻ በፊት በአያት፣ በሲኤምሲ፣ በብርጭቆ ፋብሪካ፣ በመገናኛ 24፣ በቡልቡላና በገርጂ ፈጣን የግንባታ እንቅስቃሴ ይታይ እንደነበረና የአንዳንዶቹ አፈጻጸም እንዲያውም ከእቅድ በላይ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኾኖም የቤቶቹ ቁጥር ከተመዝጋቢዎቹ ጋር በጭራሽ የሚመጣጠን አይደለም፡፡
በ40/60 መርሀ ግብር 150ሺ የሚጠጉ ተመዝጋቢዎች በቁጠባ ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ቤታቸውን ለማግኘት ከዚህ በኋላ በትንሹ ስድስት ዓመታትን መጠበቅ ሊኖርባቸው ይችላል፤ እንደ ጽሕፈት ቤቱ ባለሞያ ግምት፡፡

No comments:

Post a Comment