የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በ2007 ዓ.ም. የግብር ሥርዓቱን ተከትለው ባልሠሩ የልኳንዳ ቤቶች የግምት ታክስ እንዲከፍሉ እንደሚደረግና በቫት ሥርዓቱም እንደሚጠየቁ አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ሐምሌ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የዕቅድ አፈጻጸምና ተግዳሮቶችን ባለድርሻ ከሆኑ የታክስ ከፋዩ ተወካዮች ጋር በገመገመበት ወቅት፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ በቅርቡ የልኳንዳ ነጋዴዎች በአዲስ አበባ የፈጸሙትን የሥራ ማቆም አድማና አጠቃላይ ችግሮቹን የተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ችግሩ የተፈጠረው በቁም ከብት አቅራቢ ነጋዴዎችና በልኳንዳ ነጋዴዎች መካከል በደረሰኝ ላይ የተመሠረተ ግብይት ባለመኖሩ በመሆኑ፣ የልኳንዳ ነጋዴዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱትን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ባለሥልጣኑ በጥናት ላይ የተመሠረተ መመርያ ማውጣቱን አስረድተዋል፡፡
የቁም ከብት አቅራቢዎችን ወደ ደረሰኝ ሥርዓት ለማምጣት እየተሠራ ቢሆንም፣ ወደዚህ ሥርዓት እንዳይገቡ በሌላ አካል ጫና እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹የተደራጀ መረብ አለ፤›› ያሉት አቶ በከር፣ ይህ ቢሆንም እንኳ የልኳንዳ ነጋዴዎች ደረሰኝ ከሚያቀርቡ የቁም ከብት ነጋዴዎች ብቻ ግብይት መፈጸም እንዳለባቸው በሕግ እንደሚገደዱ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ያልተስማሙ የልኳንዳ ነጋዴዎች ግን በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ አድማ መምታቸውን አውግዘዋል፡፡ የልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ለተፈጸመው ስህተት ይቅርታ መጠየቁንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ቢሆንም በንግድ ሕጉ መሠረት በሸማቹ ኅብረተሰብ ላይ በፈጸሙት በደል ሊጠየቁ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡
በወጣው መመርያ መሠረት በ2007 ዓ.ም. የግብይት ሥርዓታቸው በደረሰኝ ያልተደገፈ የልኳንዳ ነጋዴዎች በግምት የሚጣል ታክስ እንደሚጠብቃቸው፣ እንዲሁም በቫት ሥርዓቱ መሠረት መንቀሳቀስ የሚጠበቅባቸው በመሆኑ ቫቱን ከነቅጣቱ መክፈል እንደሚገደዱ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከዚህ ሊያድናቸው የሚችል ማኅበር ያለ አይመስለኝም፤›› ያሉት አቶ በከር፣ ‹‹ማኅበሩ ራሱንም አያድንም፣ ተጠያቂ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የማኅበሩ አመራሮች የተፈጠረው ችግር ተገቢ እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ችግሩ ሊቀረፍ የሚችለው የቁም ከብት አቅራቢዎች በደረሰኝ እንዲያቀርቡ ሲደረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የልኳንዳ ነጋዴዎች የፈጸሙት የሥራ ማቆም አድማ ከማኅበሩ ጋር ግንኙነት እንደሌለው የማኅበሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ ከሁለት ሳምንት በፊት ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡ የልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበሩ መብታቸውን እንዳላስከበረላቸውና እንደሚያፈርሱትም መዛታቸው ይታወሳል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
No comments:
Post a Comment