Tuesday, April 7, 2015

በየመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን የማውጣት እንቅስቃሴ አልተጀመረም


መጋቢት ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየመን የሚካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ተጋፍጠው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉትን ከ2 ሺ ያላነሱ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያንንን
ለመመለስ እንቅስቃሴ እየታየ አይደለም ሲሉ የመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ኢምባሲው ባቀረበው ጥሪ መሰረት ምዝገባ አካሄዱ ቢሆንም ፣ መቼና እንዴት እንደሚሄዱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
አንዳንድ አገራት የባህር እና የአየር ሃይላቸውን በመላክ ዜጎቻቸውን ቢያወጡም ፣ በኢትዮጵያ በኩል ስለሚደረገው እንቅስቃሴ መንግስት አስቸጋሪ ነው ከማለት በስተቀር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
ሱዳን ዜጎቿን በአየር ለማውጣት ያደረገችው ሙከራ ከሰአነ መሪዎች የማረፍ ፈቃድ በመከልከሉዋ ሳይሳካላት ቀርቷል። ሱዳን ከሳውድ አረቢያ ጎን በመቆም በሃውዚ አማጽያን ላይ የሚደረገውን የአየር ድብደባ ከሚደግፉት አገራት መካከል ናት። ፓኪስታን ዜጎቿን በአየር
ማስወጣት የቻለች ሲሆን፣ ግብጽ፣ ቻይና፣ ሩሲያና በርካታ አገራት ዜጎቻቸውን በተሳካ ሁኔታ እያወጡ ነው። አልጀሪያና ህንድ ደግሞ ዜጎቻቸውን በሙሉ ማውጣታቸው ታውቋል።
የኢህአዴግ መንግስት በሳውድ አረብያ የሚመራውን የአየር ድብደባ ደግፎ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል። ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ከስልጣን የተባረሩት ፕ/ት ሃዲ ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዲመጡ እንደምትፈልግና ከሱዳንና ጁቡቲ ጋር
በመሆን ስለምትወስደው ቀጣይ እርምጃ እንደምትመክር ተናግረዋል። የአቶ ሃይለማርያም መግለጫ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ በየመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል በሚል ተተችቶአል።
ጦራቸውን ከአማጽያን ጎን ያሰለፉት እና የሃውዚ ሚሊሺያዎችን የሚደግፉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት አሊ አብዱላ ሳላህ ኢትዮጵያ ውስጥ በጥገኝነት ይኖራሉ። ሳላህ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ በሳውዲ የሚመራው የአየር ድብደባ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ኢህአዴግ በሳላህ ላይ ያለው አቋም ግልጽ አይደለም።
በሌላ በኩል ደግሞ የኢህአዴግ ደጋፊ የሆነቸው ቻይና በሳውዲ መሪነት የሚወሰደውን እርምጃ እየተቃወመች ነው።


Source:ethsat.com

No comments:

Post a Comment