Wednesday, August 5, 2015

ከንግድ ባንክ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በመመዝበር የተጠረጠሩ ሠራተኞችና ዘመዶቻቸው ተከላከሉ ተባሉ


ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ መዝብረዋል ተብለው በሙስና ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የባንኩ ሁለት ሠራተኞችና ዘመዶቻቸው እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባለፈው ዓመት ነሐሴ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ያቀረበውን ክስ የሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት፣ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠባቸው ተከሳሾች 13 ናቸው፡፡

የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በሒሳብ ማስታረቅ የሥራ ክፍል የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራየሁ ተክሌና የሒሳብ አስታራቂ አቶ ኤፍሬም ወልደተንሳይ፣ ዘመዶቻቸው ደግሞ ወ/ሮ ንብረት ማሞ፣ አቶ ሔኖክ ወልደተንሳይ፣ ወ/ሮ ትንሳዔ ማሞ፣ ወ/ሮ ውዳሴ ማሞ፣ አቶ ሪካርዶ ፔሪሊ ጉዶ/ገብረተክለና አቶ ዓለሙ አብርሃም ሲሆኑ፣ ከእነሱ ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀሉን መፈጸማቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ማስመስከርና ሰነዶችንም ማቅረብ መቻሉን ብይኑ ያብራራል፡፡

አቶ ንብረት ማሞ የተባሉት ተከሳሽ የባንኩ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ታምራየሁ አማች ሲሆኑ፣ የወ/ሮ ትንሳዔ ማሞና የወ/ሮ ውዳሴ ማሞ ወንድም መሆናቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ወ/ሮ ትንሳዔ ማሞም የአቶ ታምራየሁ ባለቤት ናቸው፡፡ በባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ሒሳብ አስታራቂው አቶ ኤፍሬም የአቶ ሔኖክ ወልደተንሳይ ወንድም ሲሆኑ፣ አቶ ዓለሙ አብርሃ ደግሞ የአቶ ታምራየሁ የአክስት ልጅ መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በምስክር ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ የሰጠው ብይን ይገልጻል፡፡ ተከሳሾቹ የሥጋ ዝምድናና የጋብቻ ዝምድናቸውን በመጠቀም ወንጀሉን ለመፈጸምና ሚስጥሩን ጠብቆ ለማቆየት እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀማቸውንም አክሏል፡፡

አቶ ታምራየሁና አቶ ኤፍሬም የመንግሥት የሥራ ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት የውስጥ ሒሳብ ላይ እየተቀነሰ ወደተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች መተላለፍ የሚገባቸውን የሒሳብ ማስታረቅ ሥራ እንዲሠሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ የገንዘብ ምዝበራ መፈጸማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ተከሳሾቹ ለገንዘብ ምዝበራ የሚያመቻቸውን ዘዴ ማለትም የሲስተም የግል መግቢያ ቃል (User Name) እና የሚስጥር ቁልፍ (Password) በሕገወጥ መንገድ በመጠቀም ጂቢኤስ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን፣ ንብረት ማሞ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን፣ አዳነና ቤተሰቦቹ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ አከራይ፣ ሔኖክ ወልደተንሳይ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ኪራይና ወንድማገኝ ዴዛ የሕንፃ ሥራ ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ስም በተለያዩ ጊዜያት 7,065,857 ብር በመውሰድ በመንግሥትና ሕዝብ ላይ ጉዳይ ማድረሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በሰዎችና በሰነድ ማስረጃዎች ማስረዳት በመቻሉ ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

ድርጅቶቹ በዘመዳሞቹ የተቋቋሙ መሆናቸውንም ዓቃቤ ሕግ ማስረዳቱንም ፍርድ ቤቱ በብይኑ ጠቅሷል፡፡ ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ጥቅም 22፣ 23 እና 25 ቀን 2008 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter

No comments:

Post a Comment