ኢሳት ዜና (ሃምሌ 28 2007 አ ም )
በተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎች በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃዎች ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ 6 ዲፕሎማቶች ስርአቱን በመክዳት እንደወጡ መቅረታቸው ታወቀ ።
የአገልግሎት ጊዜያቸውን በማጠናቀቅና በተለያዩ ምክንያቶች ለኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ ሀምሌ 1 2007 ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸው ለጥሪው ምላሽ በመንፈግ ስርአቱን የከዱ ዲፕሎማቶች ከአሜሪካ አፍሪካና ህንድ መሆኑን የውጪ ጉዳይ ምንጮች ገልጸዋል።
በአሜሪካ ደቡብ አፍሪካ ጋና እና ህንድ በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃዎች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩትና ከአምባሳደር እርከን በታች ሆነው ስርዓቱን የከዱት አቶ ዮሃንስ ጌታሁን (ሚኒስቴር አማካሪ) ከዋሺንግተን ዲሲ እንዲሁም ወ/ሮ እመቤት ብሩ (አታሼ) ከዋሺንግተን ዲሲ ሪፖርት ሳያደርጉ የቀሩና ስርአቱን የከዱ መሆናቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ከደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ አቶ ኤልያስ ወርቁና አቶ ጌታቸው ሙሉአለም እንዲሁም ከጋና አቶ እሸቴ ምስጋና ጥሪውን ሳይቀበሉ የቀሩና ስርአቱን የከዱ መሆናቸውን የሚገልጹት የውጪ ጉዳይ ምንጮች ሶስቱም የየአገራቱ አምባሳደሮች አማካሪዎች እንደነበሩ ታውቋል።
ከህንድ ኒውደልሂ አማካሪ የነበሩት አቶ ሄኖክ አስናቀም ከከዱት ዲፕሎማቶች ስድስተኛው ሆነው ተመዝግበዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለ71 ዲፕሎማቶች ሹመትና ስምሪት የሰጡበት ዝርዝር ለኢሳት የደረሰው ሲሆን የግዜ ገደባቸው ያልተጠናቀቀ አገር አምባሳደርም ወደ አዲስ አበባ ተጠርተዋል ።
ለኢሳት የደረሰውን የ 71 ተሿሚዎች ዝርዝር እና ተጨማሪ መረጃዎችን በቅርብ ቀን ይፋ እናደርጋለን።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment