Friday, January 22, 2016

ድንገተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ይነሳል የሚል ስጋት የገጠመው መንግስት ማረጋጊያ ያላቸውን እርምጃዎች ሊወስድ ነው


ጥር ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በታህሳስ ወር መግቢያ ላይ በጦር ሃይሎች አካባቢ በሚገኝ አንድ የደህንነት ጽ/ቤት ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑ የደህንነት አባላት በተሳተፉበት ስብሰባ ላይ ከማስተር ፕላኑ፣ ከኑሮ ውድነቱና ከሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጋር በተያያዘ ህዝቡ በድንገት ወደ አደባባይ ሊወጣ ይችላል የሚል መልእክት ተላልፏል።
በስብሰባው ላይ ለችግሩ መፍትሄ ያስገኛሉ የተባሉ በርካታ የመፍትሄ ሃሳቦች ቀርበዋል። የጦር መሳሪያዎች ያሉዋቸውን ሰዎች ተከታትሎ ከመቀማት ጀምሮ በሃይማኖት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በእስር ላይ የሚገኙትን የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ አባላት በከፊልና በአጠቃላይ መፍታት ህዝበ ሙስሊሙ ከተነሳው ወላፈን እንዲርቅ እንደሚያደርገው የተነገረ ሲሆን፣ ይህን ለማስፈጸም በውጭ አገር የሚገኙ የሙስሊም ድርጅቶች እንዲጋበዙና በታሳሪዎች ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ ማድረግ ፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ቢቻል ከማህበረሰቡ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቢሆኑ እንደሚመረጥ ስትራቴጂ ተነድፏል።
የኮሚቴው አባላት ከተቻለ በጸጥታ ሃይሎች በኩል ካልተቻለም ታስረው በተፈቱ ሌሎች ሙስሊሞች በኩል ግፊት ተደርጎባቸው ፣ የይቅርታ ጥያቄው የእነርሱ መሆኑንና የሚያመለክት ሰነድ እንዲፈርሙ ማድረግ፣ መንግስት እጁ አለበት እንዳይባል በመንግስት በኩል የተዘጋጀውን ዘጋቢ ዶክመንታሪ ለህዝቡ አስቀድሞ ማቅረብ ፣ ይሁን እንጅ መንግስት በአሸባሪዎች ላይ ጠንካራ አቋም እንዳለው ማሳየት ተገቢ መሆኑን ስትራቴጂው ያመለክታል። ይቅርታ ሊጠይቁ የሚመጡትን የውጭ እንግዶች በክብር ተቀብሎ ማስተናገድ፣ ቃለመጠይቅ ማድረግና ይህንኑ በብዙሃን መገናኛ ጉዳዩና ይቅርታው በእርግጥም የኮሚቴ አባላቱ መሆኑን ለህዝቡ ማቅርብ የሚለው አካሄድ ስልትም ተነድፏል። ይህንን ጉዳይ ለማስፈጸም ለውስጥ ጸጥታና ለጠ/ሚኒስትር ቢሮ ሪፖርት የሚያደርጉ በወ/ሮ አይጠግቡሽ ለሜሳ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የመጀመሪያውን ሂደት ለመገምገም በሚቀጥለው ሳምንት ቀጠሮ መያዙም ታወቋል። መንግስት ሙስሊሙ ማህበረሰብ በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ደግፎ እንዳይቆም የነደፈው ስትራቴጂ ውጤታማ ይሁን አይሁን በቅርቡ የሚታይ ይሆናል።
በሌላ በኩል በኦሮሚያ የተከሰተውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በተለይ በአዲስአበባ ከተማ የሚገኙ የፌዴራልና የክልል መ/ቤቶች ውስጥ የሚገኙና ቁልፍ ቦታዎችን የያዙ የህወሀት አባላት የመደናገጥና የመቧደን አዝማሚያ እያሳዩ መምጣታቸውን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ገልጿል።
ለወትሮ ፈላጭ ቆራጭ አድርገው ራሳቸውን የሾሙ የህወሀት ካድሬዎችና አባላት ለብቻ የመሰብሰብ አዝማሚያ እያሳዩ ሲሆን በተለይ የኦህዴድ አባላትን በጥርጣሬ እየተመለከቱ መምጣታቸው በድርጅቶቹ መካከል ውጥረት እያስከተለ ነው።
በአንድ የመንግስት መ/ቤት ውስጥ የሚሰራ የኦህዴድ አባል ለዘጋቢያችን “ህወሀቶች ኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ህዝባዊ አመጽ የመንፈስ ስብራት አስከትሎባቸዋል።በተለይ ደግሞ ከአመጹ ጀርባ የኦህዴድ አባላት አሉበት ብለው በማመናቸው ከፍተኛ ፍርሀትና መረበሽ እየታየባቸው ነው። ትላንት ህወሀትን ተጠግቶ ፈላጭ ቆራጭ የነበረው አንገቱን ደፍቶ ሲሄድ፣ከሌሎች የህወሃት አባላት ጋር ብቻ ሲወጣና ሲገባ ታገኘዋለህ። በመንግስት ተቁዋማት በግልጽ የዘር ልዩነቱ እያፈጠጠ መምጣቱ አሳዛኝ ነው” ሲል ተናግሮአል።
ሌላው ታዛቢም “ህወሀቶች ለብቻቸው ስብሰባ አብዝተዋል፣ሳያውቁት ራሳቸውን ከኢህአዴግ ሰዎች ጭምር እየነጠሉ ነው” ብሎአል።
የኦሮሚያን አመጽ ለማረጋጋት ሲባል የኦሮሞ ልጆች በህወሀት ደህንነትና ፖሊሶች ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ መገደላቸው በርካታ የኦህዴድ አባላትን ጭምር ማስቆጣቱ ጉዳዩ በቀጣይ የግንባሩ የልዪነት ምንጭ በመሆን ውስጣዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል።

No comments:

Post a Comment