Friday, January 22, 2016

የአለማቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የተከሰተው ረሃብ ከአቅም በላይ ነው ቢሉም መንግስት እያጣጣለው ነው


ጥር ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሪዩተርስ ዛሬ ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ አስከፊ በተባለው ረሃብ 400 ሺ ህጻናት ከፍተኛ አደጋ አንዣቦባቸዋል። አንድ አስረኛ የሚሆነው ህዝብ ራሱን መመገብ በማይችልበት ደረጃ መደረሱን ዘጋባው አመልክቶ፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ የሚሰጠው ምላሽ አነስተኛ መሆን ችግሩን አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሶታል።
በአሜሪካ የህጻናት አድን ድርጅት ፕሬዚዳንት ካሮሊን ማይልስ አፋርና አማራ ክልሎችን መጎብኘታቸውን ለዜና ምንጩ ገልጸው፣ በምግብ እጥረት የተነሳ ሆስፒታል የገቡ ህጻናትን ማየታቸውን ተናግረዋል።
በአማራ አካባቢ አንድ እናት የ3 ወር መንታ ልጆቻቸውን ማጥባት ተስኖአቸው ማየታቸውን የገለጹት ሃላፊዋ፣ መንግስት በየስድስት ሳምንቱ የሚሰጣቸው እርዳታ ለአንድ ሳምንት ብቻ የሚያቆይ መሆኑን ተናግረዋል።እርዳታው በፍጹም ህይወትን ለማቆየት የሚረዳ አይደለም በማለት መንግስት በቂ እርዳታ እየሰጠሁ ነው በማለት የሚሰጠውን መግለጫ አጣጥለውታል።
ረሃቡን ለመቋቋም 1 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቢያስፈልግም፣ የአለማቀፉ የምግብ ፕሮግራም እስካሁን ያገኘው ድጋፍ 13 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው። ድርጅቱ ለጋሽ አገራት ገንዘብ በመለገስ ከአገር ውስጥ ገበያ ገዝተው እንዲያከፋፍሉ ለማድረግ ፍላጎት ቢኖርም፣ በቂ ሸመታ ለማካሄድ የሚያስችል የእህል አቅርቦት ባለመኖሩ የምግብ እርዳታ እንዲደረግ እየጠበቁ ነው። እርዳታው አሁኑኑ ካልደረሰ ችግሩ ይባባሳል ሲል የአለም የምግብ ፕሮግራም አስጠንቅቋል።
መንግስት የውጭ ድርጅቶች እርዳታ ለማግኘት ሲሉ ችግሩን አጋነው እያቀረቡት ነው በማለት ወቀሳ ያቀርባል። የመንግስት መግለጫ የአለማቀፍ ማህበረሰቡ አፋጣኝ መለስ እንዳይሰጥ ማድረጉን ታዛቢዎች ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment