ጥቅምት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ በሽብረተኝነት ወንጀል የተከሰሱት አቶ ደህናሁን ቤዛና አቶ ምንዳዬ ጥላሁን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ቀርበው እንዲመሰክሩ ፍርድ ቤቱ ለተለያዩ አካላት ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ለልደታ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት በድጋሜ ደብዳቤ ጽፈዋል።
ቃሊቲ እስር ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፣ ቃሊቲ አለመታሰራቸውን ጥቅምት 12 ፣ 2008 ዓም ለፍርድ ቤቱ ጠቅሶ የነበረ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ ግን የቃሊቲን እስር ቤት ምክንያት ባለመቀበል ፍርድ ቤቱ ለተለያዩ አካላት ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው ጠይቀዋል።
ነገረ ኢትዮጵያ በለቀቀው የጽሁፍ ማስረጃ፣ እስረኞቹ ” የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መያዙን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬት መግለጫ መስጠቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መስከረም ወር 2007 ዓ.ም የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን መያዝ፣ የእድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ መሆናቸውን በመግለፅ የኢትዮጵያ መንግስት ፍርዱን ተፈፃሚ እንደማያደርግ መግለፃቸውን እንዲሁም በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ አቶ አንዳርጋቸው ዜግነታቸው እንግሊዛዊ በመሆኑ ክትትል እንደሚያደርግ ” በመግለጽ፣ ፍርድ ቤቱ ለእነዚህ ሶስት አካላት ድብዳቤ እንዲጽፍላቸው ፍርድ ቤቱን አስጨንቀውታል።
አቶ አንዳርጋቸው መሰረታዊ የሚባሉትን መብቶቻቸውን እንዳያገኙ ተከልክለው ቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ ይገኛል። አቶ አንዳርጋቸው ህክም እንዲያገኙ እና የህግ ባለሙያ እንዲናግራቸው ቢጠይቁም አልተፈቀደላቸውም። ከሁለት እስረኞች ጋር አብረው የተሳሩት አቶ አንዳርጋቸው፣ አያያዛቸው አስከፊ መሆኑን ሊጠይቁዋቸው ለሄዱት የእንግሊዝ አምባሳደር በቅርቡ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ አቶ አንዳርጋቸው አሁንም በጠንካራ መንፈስ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሎአል።
በሌላ ዜና ደግሞ ከቀረበባቸው የሽብር ክስ ነጻ የተባሉት የአንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ከተጠየቀባቸው በሁዋላ አሁንም በድጋሜ ለጥቅምት 22/2008 ተቀጥረዋል። አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና አብርሃም ሰለሞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ነጻ ቢላቸውም ሊፈቱ አልቻሉም።
እነ አቶ ሃብታሙ በአካል ያልቀረቡ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ያልቀረቡበትን ምክንያት ሲጠይቅ፣ የቂልጦና ቃሊቲ እስር ቤቶች ተወካዮች ፣ ሂደቱ ቃሊቲ በፕላዝማ ይታያል ስለተባለ አላቀረብናቸውም የሚል መልስ ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱም ‹‹ይሄ ቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚባል ነገር የሚሆን አይደለም፤ አቅርቧቸው ብለን አዝዘን ነበር፤ እኛ ነን የምናዝዛችሁ ወይስ ማን ነው? አሁንም ቀጣይ ቀጠሮ ላይ አቅርቧቸው›› ሲል ትዕዛዝ መስጡን ጋዜጣው ዘግቧል።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment