Thursday, April 9, 2015

የመንግስት አመራሮችና ጋዜጠኞች ከውጭ እና ከውስጥ የሚለቀቀውን ፕሮፖጋንዳ እንዲያከሽፉ አደራ ተጣለባቸው


መጋቢት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ኢህአዴግ የኒዮ ሊበራል አፈቀላጤ የሚላቸውን እነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማንራይት ዎች እና ሲፒጄ የሚያወጡትን መግለጫ ነቅቶ በመጠበቅ አፍራሽ ጎናቸውን እንዲያጋልጡ አደራ ተጥሎባቸዋል፡፡
የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት፤ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አዘጋጆችና አመራሮች ለሶስት ቀናት በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ ከምዕራባዊያን ሀገራት የሚፈልቁ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳዎችን በማጋለጥ ጋዜጠኞች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አደራ ተጥሎባቸዋል፡፡
የኒዮሊበራል ኃይላት አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የመንደር ማሰባሰብ መርሃግብር፣ የስኳር ፕሮጀክቶች፣ ለግብርና ልማት የሚሰጡ ሰፋፊ እርሻዎች፣ የጊቤ ሶስት ፕሮጀክት፣ የህዳሴ ግድብ፣ እንዲሁም በስራ ላይ ካሉት ሕጎች መካከል
የጸረሽብር ሕጉ፣ የበጎ አደራጎትና ማህበራት አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት ሕግ፣ በሀገር ውስጥ ሕጋዊውንና ሕገወጡን መንገድ ያጣቅሳሉ የተባሉት ሰማያዊ፣ መድረክ እና መሰል ፓርቲዎች የሚለቁትን ፕሮፖጋንዳ እንዴት ተከታትለው ማክሸፍ እንደሚገባቸው  ትምህርታዊ ማብራሪያ ተሰጥቶአቸዋል፡፡
የኒዮሊበራል ሃይላቱ እነዚህን አጀንዳዎች መሰረት አድርገው የማጥላላት ዘመቻ ሊከፍቱ ስለሚችሉ ተከታታይነት ባለው መልኩ ምላሽ መስጠትና የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ አንቅሮ እንዲተፋቸው መገናኛ ብዙሃኑ በቅንጅትና ተከታታነት ባለው መልኩ ሊሰሩ
እንደሚገባ ተነግሮአቸዋል፡፡
የኒዮሊበራል ሃይላቱ እነዚህን ክስተቶች መነሻ በማድረግ በሕዝብና በመንግስት መካከል አለመተማመን በመፍጠር በሀገሪቷ አለመረጋጋት እንዲፈጠር  የተቀናጀ ድብቅ ኣላማ እንዳላቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ አስቀድመው መረዳት አለባቸው ተብሎአል፡፡
በኒዮሊበራል ሃይላት የሚነሱት አጀንዳዎች ተደጋጋሚ በመሆናቸው የመንግስትን ምላሽ የያዘ ሰነድ መዘጋጀቱ የተጠቆመ ሲሆን ፣መገናኛ ብዙሃኑ ሰነዱን እያጣቀሱ እንዲሰሩ በማሳሰብ ስልጠናው ዛሬ ተጠናቆአል፡፡

Source: ethsat.com

No comments:

Post a Comment