ማስመጥ! የኮንትሮባንድ ትርጉሙ ምንድነው?
በሻሸመኔ አካባቢ የኮንትሮባንድ ንግድ ተቋማዊ ቅርጽ መያዙን የሚያሳይ መረጃ ጠቆመ፡፡ ሌሎች በኮንትሮባንድ ንግድ እንዳይሳተፉ የሚከለክለው ሕግ የሚጸናባቸው ከህወሃት ራቅ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸው ድርጊቱን “ማስመጥ” አሰኝቶታል፡፡ ዜጎችም “የኮንትሮባንድ ንግድ ትርጉሙ ምን ይሆን?” እያሉ ነው፡፡
የኮንትሮባንድ ንግድ በህጋዊነት በተለይ የሚፈጸመው ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም ላለፉት 25 ዓመታት በግፍ እየገዛ ባለው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግምባር ህወሃትና በአፍቃሪዎቹ መሆኑን በማረጋገጥ የጎልጉል እማኝ ዘጋቢ (ireporter) በዓይን ምስክርነት የታዘቡትን በፎቶ የተደገፈ መረጃ ልከውልናል፡፡ ዜናውን እማኝ ዘጋቢው ይላኩት እንጂ በድፍን አገሪቱ ህወሃቶች፣ የህወሃት አገልጋዮች፣ የህወሃት ሽፋን ሰጪዎች፣ ነባር ተጋዳላዮች፣ ተላላኪዎች፣ ወዘተ በዚህ ሥራ እንዲሰማሩ የተፈቀደላቸውና የይለፍ ካርድ/መታወቂያ የተሰጣቸው ናቸው፡፡
ከእማኝ ዘጋቢው ጋር በተደጋጋሚ በተላላክነውና ባጠናቀርነው መረጃ መሠረት ጉዳዩ እየተፈጸመ ያለው በሻሸመኔ ከተማ ነው፡፡ ዘጋቢውሁኔታውን በማስመልከት እንዴት የህወሃት ድጋፍ ባለው መልኩ የኮንትሮባንድ ንግዱ እንደሚካሄድ ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ፡-
“ይኼ የላኩላችሁ ፎቶ በሻሸመኔ ከተማ በጠራራ ጸሃይ በህወሃት እየተካሄደ ያለው ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ነው፤ … እነዚህ ሰዎች ያለ ማንም ከልካይ ዕቃ ከሞያሌና ከዶሎ (ሶማሌ ክልል በነጌሌ ቦረን በኩል) በአይሱዙ ይጭናሉ፡፡ መንገድ ላይ ያሉትን የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ኬላዎችን ያለ አንዳች ከልካይ ያልፋሉ፤ (ኬላ ላይ ሲያቆሟቸውም) just በትግሪኛ ያወሯቸዋል፤ ግፋ ቢባል የሆነች ብጣሽ ወረቀት ያሳያሉ፤ ይቺ ወረቀት የምትለው ደግሞ አባል ስለሆኑ ይለፉ ነው፤ … የህወሃት ማኅተም ተመቶበታል፡፡ በቃ ሁሉንም ኬላዎች ያልፉና ሻሸመኔ በግላጭ ያራግፋሉ፤” በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡
በኮንትሮባንድ ያስገቡትን ዕቃ መጠን እና የት እንደሚያከማቹ ሲገልጹ ደግሞ፤
“… ቢያንስ በሳምንት አራት FSR Isuzu በእያንዳንዱ መጋዘናቸው ያራግፋሉ፤ እኔ እንኳን የታዘብኩት ሰፈሮች ደግሞ ከሚካኤል ቤ/ክ ወረድ ብሎ 07 እና 08 ቀበሌዎች አራት መጋዘኖች አሏቸው፡፡ አንደኛው ከሸገር አሮጌ ጫማ ማደሻ ወረድ ብሎ 3ኛው ግቢ ውስጥ ሲገኝ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ከአንደኛው ግቢ 200 ሜትር ወረድ ብሎ ከሚገኘው furniture ቤት በቀኝና በግራ ያሉት ግቢ ውስጥ ነዉ። አራተኛው ማከማቻ 08 ቀበሌ ተክሌ ቦጋለ የሚባል ባለ አንድ ፎቅ pension ግቢ ውስጥ ነው። (ከእነዚህ ማከማቻዎች በተጨማሪ) ሸዋ በር በሚባል አካባቢ 3 መጋዘኖች አሉ፡፡ አንደኛው ዘቢብ ሆቴል፤ ሁለተኛው መናፈሻ ጊቢ ውስጥ ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ የዱሮው እንጆሪ ጊቢ ውስጥ ናቸው፤ … እነዚህ ቡድኖች እንደዚህ ወንጀል እየሠሩ ማንም አይናገራቸውም፤ … ነገር ግን የሌላ ብሔር ተወላጅ ድንገት አንዲት ፌስታል ሰልባጅ ከተያዘበት 7 ዓመት ተፈርዶበት ወኅኒ ይወርዳል፤ … በዚህች አንድ ወር እንኳን 4 ልጆች ተፈርዶባቸው እስር ቤት ወርደዋል፡፡”
በዚህ የኮንትሮባንድ ንግድ የተሰማሩት የህወሃት ባለፈቃዶች የሚያስገቡት ዕቃ “በአብዛኛው ሰልባጅ ልብሶች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ አረቢያን መጅሊስ፣ ቶርሽን ጫማዎችና የመሳሰሉት” መሆናቸውን ስማቸው እንዳይነገር የጠቀሱት እማኝ ዘጋቢው አስረድተዋል፡፡ ሲቀጥሉም “ይህንን ስራ በንደዚህ መልኩ በገሀድ መስራት ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በላይ” እንደሆናቸው ዘጋቢው ሲያስታውቁ “በተለይ ከአንድ አመት ወዲህ ደግሞ ቁጥራቸው እጅጉን በጣም” እየጨመረ እንደመጣ እማኝነት በላኩልን መረጃ አስታውቀዋል፡፡ የህወሃት ውክልና እና ፈቃድ የተሰጣቸው “ልማታዊ ኮንትሮባንዲስቶቹ” በከተማው ዕቃውን ለመሸጥ ሱቅ እንደሌላቸው ነገር ግን የኮንትሮባንድ “እቃውን ካስገቡ በኋላ ለነጋዴዎች በጅምላ ለተጠቃሚ ደግሞ በችርቻሮ … እዛው እቃው ባለበት ግቢ” ውስጥ እንደሚሸጡ የዓይን ምስክር ነኝ በማለት ለጎልጉል ከሥፍራው በፎቶግራፍ የተደገፈ መረጃ የላኩልን እማኝ ዘጋቢ አስረድተዋል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ መሰል ሕገወጥ ንግዶች በህወሃቶች እንደሚፈጸም ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡ በተቋማዊ መልክ በአገሪቱ ውስጥ ስለተንሰራፋው ሕገወጥ ንግድ እና በድርጅት ፈቃድ እና ዋስትና ስለሚካሄደው የኮንትሮባንድ ንግድ የጸረ ሙስና ኮሚሽንን መጠየቁ ከኮሚሽኑ አፈጣጠር፣ ዓቅምና ህልውና በላይ ይመስለናል፡፡ በህወሃት አገዛዝ ውስጥ ህጋዊ የሆነ ህገወጥነት አለ፤ ህገወጥ የሆነ ህጋዊነት አለ፡፡ ተቋማቱ ሁሉ የሚሠሩት በዚህ ባልተጻፈ ወይም ባልተደነገገ መመሪያ ስለሆነ “ማጣራት” የሚባለው ነገር አቅመቢስ፣ ዋጋቢስ ነው፡፡
ጎልጉል የእማኝ ሪፖርተሮች ያሉት ሲሆን በነዚሁ ምንጮቹ አማካይነት መረጃ ለህዝብ ሲያቀርብ የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ለዚህም ነው “ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ ነው” የምንለው፡፡ ይህንን ዜና ተመለከተ ከአገዛዙ አካላት ምላሽ ለመስጠት ድፍረት ወይም ብቃት ያላቸው ካሉ ለዝግጅት ክፍላችን ሊልኩልን ይችላሉ፡፡
No comments:
Post a Comment