Wednesday, October 21, 2015

ኢትዮጵያ ተጨማሪ ገንዘብ ከግል ባንኮች ልትበደር ነው


ጥቅምት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ረዩተርስ እንደዘገበው የኢህአዴግ መንግስት ባለፉት 10 ወራት 1 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ20 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ገንዘብ ከግል የውጭ አበዳሪ ባንኮች ከተበደረ በሁዋላ፣ አሁን ደግሞ 2 ቢሊዮን ዶላር ወይም 40 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመበደር በድርድር ላይ መሆኑን ረዩተርስ ዘግቧል።
አዲሱ ብድር የኢትዮጵያን እዳ ከ32 ቢሊዮን ዶላር ወይም ከ1 ትሪሊዮን 40 ቢሊዮን ብር በላይ ያደርሰዋል። የአለማቀፍ የገንዘብ ተቋም በየጊዜው እየቸመረ የሚሄደው የኢትዮጵያ ብድር አሳሳቢ መሆኑን በቅርቡ ገልጿል። መንግስት ከግል ተቋማት መበደራችን የእድገታችን ውጤት ነው በማለት ይከራከራል። ከግል ተቋማት የሚገኘው ብድር ከሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ወይም አለማቀፍ የልማት ድርጅቶች እንደሚሰጠው ብድር አይሰረዝም።
መንግስት አሁን ለሚወስደው ዩሮ ቦንድ እየተባለ ለሚጠራው ብድር 6 ነጥብ 6 በመቶ ወለድ ይከፍላል። ብድሩ ለ10 አመታት የሚቆይ ሲሆን፣ አገሪቱ በአጠቃላይ በ10 አመታት ውስጥ 210 ሚሊዮን ዶላር ወይም 4 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ብር ወለድ ትከፍላለች።
ፋይናንሻል ታይምስ ባወጣው ዘገባ ደሃ አገሮች አበዳሪ ስላገኙ ብቻ የሚበደሩት ገንዘብ በሁዋላ እነሱን መልሶ እንደሚጎዳቸው አስጠንቅቋል። የኢኮኖሚ እድገቱ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች ቢቀዘቅዝ፣ ብዱን ለመመለስ አስቸጋሪ እንደሚሆንና አበዳሪ የግል ተቋምት ገንዘባቸው እንደሚመለስላቸው ከፈለጉ በጥንቃቄ እንዲያበድሩ መክሯል። ዘ ኒዮርክ ታይምስ እንደገለጸው 2 ቢሊዮኑ ዶላር በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ሊሰጥ ይችላል።
መንግስት ወደ ውጭ የሚልከው ምርቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት አጋጥሞታል። ይህንን እጥረት ለመሸፈን ብድርን እንደዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እየተጠቀመበት ነው ሲሉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
አገሪቱ አብዛኛውን የውጭ ምንዛሬ በእርዳታና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ከሚልኩት ገንዘብ ታገኛለች።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment