Wednesday, October 21, 2015

በአዲስ አበባ በርካታ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ድርጅቶች እየፈሩሰ ነው


ጥቅምት ፲ (አስር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደገለጹት በአሜሪካ ጊቢ ፣ በአዲስ ከተማና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለአመታት ከኖሩበት ቤት ያለበቂ ካሳ እና ተለዋጭ ቤት ቤቶቻቸው እየፈረሰባቸው ነው።
መንግስት ቤታቸው ለሚፈርስባቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ተላዋጭ አድርጎ ቢሰጥም፣ ተከራዮች ግን ኪራዩን የመክፈል አቅም የላቸውም መንግስት ከህዝቡ ጋር ሳይማከር የሚወስደው እርምጃ፣ ከፍተኛ የኑሮ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑን ነዋሪዎች በምሬት ይናገራሉ በተመሳሳይ ዜና ደግሞ የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ የቀድሞ ኪራይ ቤቶች አስተዳደር በስሩ የሚገኙ ወደ 17 ሺ የሚጠጉ ቤቶች ቢኖሩትም ከግማሽ የማያንሱት መብቱ በሌላቸው ነዋሪዎች በመያዙ ለባለስልጣናትና ለሹማምንቶች አዲስ ቤት ለመስጠት ባለመቻሉ ምክንያት ቤቶቹን ከነዋሪዎች ለመረከብ ማቀዱ ተሰምቷል፡፡ የቤቱ ተከራዮች እንፈናቀላለን በሚል ከባድ ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡
የኤጀንሲው ምንጮች እንደተናገሩት በአዲስአበባና በክልሎች ከ17 ሺ በላይ ቤቶች ኤጀንሲው ያሉት ሲሆን፣ እነዚህ ቤቶች በተፈቀደላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ወይንም ሹማምንት መያዝ ሲገባቸው ፣መብቱ በሌላቸው ሰዎች በመያዛቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት ለአዲስ ተሿሚዎች የመኖሪያ ቤት ለመስጠት አልተቻለም ፡፡
ይህን ተከትሎም ቀደም ሲል መብቱ የነበራቸው ነገርግን ከሃላፊነታቸው የተነሱ፣ ጡረታ የወጡ፣ የተዛወሩ ወይንም በሞት የተለዩ ተከራዮች የተረከቡትን ቤት መመለስ የሚገባቸው ቢሆንም፣ ቤቶቹን ካለመመለሳቸውም በተጨማሪ ለሌሎች ሶስተኛ ወገኞች በውክልና በማስተላለፍ፣ ቁልፍ በመሸጥ በሕገወጥ መንገድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡ እነዚህ ወገኖችን በአስቸኳይ ውል አቋርጦ ቤቱን ለመረከብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኤጀንሲው ምንጭ አስታውቀዋል፡፡
ኤጀንሲው ቤት ወደማስለቀቅ እርምጃ ሲገባ ከህብረተሰቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል የፌዴራል ፖሊስ ድጋፍ መጠየቁም ታውቆአል፡፡
አጀንሲው በአሁኑ ወቅት ለማንኛውም ነዋሪ ቤት የማከራየት ግዴታ እንደሌለበትና ግዴታ ያለበት ለተፈቀደላቸው የመንግስት ሹማንምንት ቤት ለማከራየት መሆኑን የጠቀሰው ምንጭ፣ ከዚህ ውጪ በታሪክ አጋጣሚ ቤት የያዙ ሰዎች በሒደት እንዲለቁ መደረጋቸው የማይቀር ነው ብሎአል፡፡
የመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ በስሩ ያሉትን የቤቶች ቁጥር እንኳን በቅጡ ባለማወቁ አንዳንድ ሰዎች የመንግስት ቤት በስማቸው እስከማዛወር የደረሱበት ክስተት አጋጥሟል።
አንዳንድ ያነጋገርናቸው የኤጀንሲው ቤት ተከራዮች በሰጡት አስተያየት በቤቶቹ ውስጥ ከ25 ዓመታት በላይ መቆየታቸውን በመጥቀስ ፣ ምትክ ቤት ሳይዘጋጅላቸው እነሱን አስወጥቶ ባለስልጣናትን ለማስገባት የታቀደው ነገር እውነት ከሆነ አሳዛኝና ኢትዮጵዊነትን የሚያስጠላ አስነዋሪ ተግባር ነው ሲሉ ኮንነውታል፡፡
እነዚህ መብት የላቸውም የተባሉ ዜጎች፣ በአገራቸው ቤት የመከራየት መብት ያላቸው ሲሆን፣ ለመንግስት ባለስልጣናት ለመስጠት ተብሎ መፈናቀላቸው በፖለቲካ ሹመኞችና በተራው ዜጋ መካከል ያለውን ልዩነት ያመላክታል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment