ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ስብሰባ አውካችሁዋል በሚል ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ማህበራዊ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አለነ ማህፀንቱና የቀድሞ የፓርቲው አባል አቶ እስማኤል ዳውድ መከላከያ ምስክሮቻቸውን ሳያሰሙ እንደተቀጠሩ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡
አቶ እስማኤል ዳውድና አቶ አለነ ማህፀንቱ እስር ቤቱ” መኪና ላገኝ ስላልቻልኩ” ተከሳሾቹን ላቀርብ አልቻልኩም፤ በማለቱ የተነሳ መዝገባቸውን እየተመለከተ የሚገኘው የአራዳ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት 5ኛ ወንጀል ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷቸዋል፡፡ እስማኤል ዳውድ ለጥቅምት 25 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው ሲሆን፣ አቶ አለነ ማህፀንቱ ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ተቀጥረዋል።
አቶ እስማኤል ዳውድም ሆነ አለነ ማህፀንቱ መንግስት አይኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ስብሰባን አውካችኋል›› በሚል ለእስር መዳረጋቸው አይዘነጋም ሲል ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል አቃቢ ህግ በዞን ዘጠኝ ጸሃፊዎች ላይ በ ፌደራል ጠ/ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቋል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጸሃፊዎቹ አሸባርዎች ለመሆናቸው ጠንካራ ማስረጃ አለ በማለት ለአለማቀፍ ሚዲያ ተናግረው ነበር። ነገር ግን ማስረጃቸውን በፍርድ ቤት አቅርበው ለማሳየት ባለመቻላቸው፣ የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት ላይና በአገዛዙ ላይ ትችታቸውን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment