Sunday, October 18, 2015

የመቶ አመቱ የቤት ስራ – ይገረም ዓለሙ


በቅድሚያ ፤ ብዕር እንደ ጠብ -መንጃ ታይቶ፤ መጻፍ አሸባሪ አሰኝቶ ለእስር የበቁት የዞን 9 ጦማሪያን ነጻ የመባላቸው ዜና አስደሳች ነው፡ይሁን እንጂ የእስር ቤቱን ቅጥር አልፈው እስካልወጡ ድረስ እነርሱንም ሆነ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ተሞክሮአችን አያስችለንምና እስኪወጡ መጠበቅ ሊኖርብን ነው፡፡

ከመነሻው ነጻነታቸው የሚታወቀው ጸኃፍት ነጻነት ዛሬ ይበልጥ የተረጋገጠ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ከዚህ በኋላ ለመከራከር የሚደፍር የሚኖር አይመስለኝም፡፡ በቂ ማስረጃ አለን በማለት ሲፎክሩ የነበሩት አቶ ኃይለማሪያምን ጨምሮ፡፡

አነጋጋሪ የሚሆነው ግን ይህ ፍርድ የተሰጠው በችሎቱ ነጻነትና በዳኞቹ ድፍረት፤ወያኔ የሚፈልገውን ስለፈጸመ፤ተቃውሞው ስለበረታ፤ አቅጣጫ ለማስቀየስና ወቅታዊውን ትኩሳት ለማብረድ፤ወይንስ ሌላ የሚለው ነው፡፡ በመሆኑም የችሎቱን ውሳኔ በጥለቀት ልናየውና ከምንደሰትበት በላይ ልንማርበት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ወደ ዛሬ ጉዳየ ልግባ፡፡

እንደ ዛሬው ሳይሆን ወያኔና ሻዕቢያን መለየት በማይቻልበትና ሁለቱም አስመራና አዲስ አበባ ቤተ መንግስት መግባታቸው የፈጠረባቸው የፖለቲካ ስካር ባልተነነበት ወቅት ኢትዮጵያውያንን ተውአቸው የመቶ አመት የቤት ስራ ሰጥተናቸዋል ማለታቸውን የምንረሳው አይመስለኝም፡፡ ያ ሰጥተናቸዋል ያሉት የቤት ስራ ብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብለው በፈጠሩልን ልዩነት ተከፋፍለንና በየመንደራችን ተቧድነን ልዩነት እንድናቀነቅን፣ ከትናንት የሀገራችን ታሪክ ለማለያያ ያስችላል ብለው እየመዘዙ የሚነግሩንን እየተቀበልን እንድንነታረክ፣በትናንት ተሸብበን በርስ በርስ ጥላቻ ተጋርደን ለዛሬ ምንም እነዳንሰራና ስለ ነገ አሸጋግረን እንዳናይ የሚያደርገን ነው፡፡ እኛ በዚህ በተሰጠን የቤት ስራ ተጠምደን ሰንዳክር እነርሱ የጫካ ስምምነታቸውን ከቤተ መንግሥት ሆነው ተግባራዊ ሊያደርጉ፤ የደም ትስስራቸውን በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያጠብቁና ሊያስጠብቁ ያለሙትም ነበር፡፡ ነገር ግን ፈጣሪ ኢትዮጵያን የዘነጋት ቢመስልም ጨርሶ አይረሳትምና እኛን እያጋጩ ሊኖሩ ያሰቡ እነርሱው ተጋጩና 10 አመትም ሳይቆዩ አያሌ ህይወት ለቀጠፈ የከፋ ጦርነት ተዳርገው ፍቅራቸው ያልበጀን በጠባቸው ለእሊቂት ዳረጉን፡፡

ወያኔ ከዛ ተምሮ ከጫካ ቅዠቱ ይወጣል፣ ከዘር ልክፍቱ ይገላገላል፣ ተብሎ ሲጠበቅ ከጦርነቱ እፎይታ ባገኘ ማግስት ይበሱን ባሰበት፡፡ ጦርነቱ አስገድዶት የዘመረውን አንድነት ረስቶ በጎሰኝነቱ ገፋበት፤ ያመነውን የኢትዮጵያን የረዥም ዘመን የነጻነት ታሪክ መልሶ ካደ፣ የጦርነቱን ድል የኢትዮጵውያን ሳይሆን የራሱ አደረገ፡፡ ከሻዕቢያ ጋር በጋራ የሰጡንን የመቶ አመት የቤት ስራም ለብቻው ቀጠለበት፡፡ ይሄው ተግባሩም በሥልጣን ለመቆየት አበቃው፡፡

ወያኔ ይህን ማድረጉ ከዚህ ውጪ በሥልጣን መቆየት እንደማይችል በማወቁ፣ ለሱ ሥልጣን በህዝብ ፈቃድ ከኮሮጆ ውጤት የሚገኝ ሳይሆን የሞት ሽረት ጉዳይ በመሆኑ፤ከልዩነት አንጂ ከአንድነት፤ ከጸብ እንጂ ከፍቅር የማያተርፍ በመሆኑ ነውና ወያኔን በቅጡ እስካወቅነው ድረስ ትናንት የፈጸማቸውም ሆኑ ዛሬም ሆነ ነገ የሚፈጽማቸው ድርጊቶቹ ብዙም የሚያስገርሙን አይደሉም፡፡ ሊሆኑም አይገባምም፡፡

ከማስገረም አልፎ አነጋጋሪና ጥያቄ አጫሪው ጉዳይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህን የወያኔን የመቶ አመት የቤት ስራ ተግባራዊ በማድረግ ለወያኔ እድሜ መርዘም አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ያውም ወያኔን በመቃወም መስዋዕትነት የሚከፍሉ ወይንም ተቀዋሚ ነን የሚሉ ወገኖች ጉዳይ ነው፡፡

የወያኔን አገዛዝ እንቃወማለን ብለው ፓርቲ መስርተውም ሆነ በየግላቸው አየታገሉ እንደሚገኙ የሚናገሩ ወገኖች ከትናንት ታሪካችን በጎውን አዳብረን በጎ ካልሆነው ተምረንና ተራርመን የትናንቱ ጥፋትም ሆነ ስህተት ዛሬ እንዳይደገም በመንገዳችንም ላይ አንቅፋት እየሆነ እንዳያስቸግር ወደ ትውልድም አንዳያሸጋገር ማድረግ የሚቻልበትን መላ ሊመቱ በተገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ወገኖች በአያት ቅድመ አያቶቻችን ግዜ የተሰሩ ተብለው የተጻፉ ወይንም የተወሩ ነገሮችን እየመዘዙ መካሰስ መወቃቅስን ስራ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ይህም የወያኔን የመቶ አመት የቤት ስራ መስራትና እንቃወመዋለን ለሚሉት ሀይል እድሜ መርዘም መጠቀም ነው ፡፡

ትኩረቱን ምርጫ 2007 ላይ አድርጎ ረገብ ያለ መስሎ የነበረው በዛሬ ላይ ሳይሆን በትናንት ትናንት በስቲያ ድርጊቶች ላይ መነታረክና ሲብስ መዘላለፍ ከምርጫው በኋላ ተባብሶ ቀጥሎአል፡፡ ከዛ በፊት ብዙም ጎልቶ አይሰማ የነበረ አማራነትም ተስፋፍቷል፡፡በማህበራዊ መገናኛዎች የሚጻፉትን ለተመለከተ አንዳንዶች ሌት ተቀን የሚያስቡት ስለ ልዩነት ይመስላል፡፡

ኢትዮጵያ ለሶስት ሺህ ዘመን የዘለቀው የነጻነት ታሪኳ ምንም እንከን ያልነበረበት ነው ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም፡፡በታሪክ ውስጥ ለጥሩውም ሆነ ለመጥፎው ግንባር ቀደም ተጠቃሾች መኖራቸውም አሌ አይባልም፡፡እነዛ አባት እናቶቻችን ደግሞ አልፈዋል፡፡ እናም በጎ ተግባራቸውን እያወደስንና አጠንክረን እየቀጠልን ለትውልድ አንዲተላለፍ ማድረግ ፣ጥሩ ላልነበረው ታሪካችን ደግሞ አሁን ተጠያቂም ተከሳሽም የሚሆን የለምና ሂሳብ ለማወራረድ ሳይሆን ለመተማመንና ለዛሬ መንገዳችን አንቅፋት እንዳይሆን፤ ለትውልድም እንዳይተላለፍ ለማድረግ አንድ ቦታ ለማቆም የሚያስችል መላ መምታት ነው የሚበጀው፡፡

ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ ሲያቅት ወይንም የነበሩ ችግሮችን አግዝፎና አክፍቶ በማውራት ትርፍ የሚገኝ መስሎ ሲታሰብ ስራው ሁሉ የመፍትሄ ሀሳብ ሳያቀርቡ እነዛኑ ችግሮች መልሶ ቀልሶ ማውራት ይሆናል፡፡ ይህን በማድረግ የወያኔን እድሜ ከማራዘም ውጪ አንድ ስንዝር ውጤት ባለፉት ሀያ አራት ኣመታት አልታየም፡፡ነገር ግን ሂደቱ ቀጥሏል፡፡ እንደውም በአደገኛ ሁኔታ ወደ ወጣቱ ተሸጋግሯል፡፡

የትናንት ድርጊት ለአሁኑ ትውልድ መማሪያ እንጂ መነታረኪያ መሆን አልነበረበትም ፡፡ ትናንት ለዛሬ መጥፎውንም ሆነ ጥሩውን አውርሶ አልፏል፡፡ ሀገር የሚያድገው ከትናንት ጥሩውን አዳብሮ መጥፎውን አርሞ፤የጎደለውን አሟልቶ፤ ከዘመኑ ጋር እየተራመዱ በመስራት እንጂ የትናንቶቹ በዘመናቸው የሰሩትን እያነሱ በመውቀስና በመካሰስ አይደለም፡፡

መክሮ የሚመልስ ሽማግሌ ጠፍቶ፤አስተምሮም ሆነ ገዝቶ የጥፋትን መንገድ የሚያስቆም የሀይማኖት አባት ከእየእምነቱ ታጥቶ፤ በትናንት ታሪክ ተግባብቶ ለዛሬ ተግባር መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል ተግባር የሚከውኑ ምሁራንና ፖለቲከኞች አልታይ ብለው ወዘተ ስራችን በአብዛኛው ካለፈውና ካለው የበሳ ችግር ሊያመጣ የሚችል ሆኗል፡፡

ልዩነታችን ጌጣችን፣ አንድነታችን ኃይላችን መሆኑን አምነን በጋራ ሊያስኬደን የሚችል የመስማሚያ መንገድ ከመቀየስ ይልቅ ሆድና ጀርባ የሚያደርገንን ነገር መፈለጉ ለምን እንደሚቀለን ግራ ያጋባል፡፡ ከየትውልድ ድርሻን አንዱንም ሳንከውን ሌላው ቢቀር ነጻነቷ የተከበረ ዳር ደንበሯ የታፈረ ሀገር ያቆዩንን አያት አባቶቻችንን ለማውገዝና በእነርሱ የተሰራውን ለመኮነን ልበ ሙሉ ደፋሮች መሆናችን ያስገርማል፡፡ ከአባቶቻችን የተረከብናትን ሀገር የህግ የበላይነት የተረጋገጠባትና ሰብአዊ መብት የተከበረባት ዴሞክራሲያዊት ሀገር ማድረግ ቀርቶ በተረከብናት ወርድና ስፋት ማቆየት ያልቻልን ትውልዶች የትናንቶቹን ለመውቀስ ለመክሰስ አንዴት እንደፍራለን፡፡ ዛሬ ሊኖረን የሚገባውን መልካም ግንኙነት ትናንትን እየጠቀስንና እያወሳን ማበላሸትና በጥርጣሬ እየተያየን ሆድና ጀርባ ሆነን እንድንቆም ስናደርግ ወያኔ የሰጠንን የመቶ አመት የቤት ስራ እየሰራን መሆናችንን አስበነው እናውቅ ይሆን፡፡

ስነ ልቦናችንን ያጠናው ደካማ ጎናችንንም የተረዳው ወያኔ በየግዜው አዲስ የሚመስሉ ግን ያልሆኑ ነገሮችን እየሰጠን፤ እንዲሁም እኛኑ መስለው ቁስላችንን እያከኩ የሚያደሙ አርበኞችን በመካከላችን እያስገባ፤ ልዩነታችን አንዲሰፋ ቅራኔያችን አንዲባባስ በማድረግ እድሜውን አስረዝሟል፡፡

በምንም ሁኔታ ግን ለዚህ ተግባራችን ወያኔን ተጠያቂ ማድረግ የለብንም፡፡ ምክንያቱም የመቶ አመት የቤት ስራ ሰጥቻቸዋለሁ ሲል ምን እንደሆነና እንዴትና በምን ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚያደርገው ተገንዝቦ ከወጥመዱ ማምለጥ የእኛ ድርሻ ነውና፡፡ ይም ቢቀር ሀያ አራት ዓመት ቀላል ግዜ አይደለምና በተግባር ከሚፈጽመው ተረድተን ከራሳችን አድራጎትም ተምረን የወያኔን የቤት ስራ በመስራት ለእሱ ዕድሜ አራዛሚ ካደረገን ተግባራችን መታቀብ መቻል የእኛ ስራ ነውና፡፡

ስለሆነም በትናንት እየተነታረክን የዛሬ መንገዳችንን ከማደነቃቀፍና የነገውንም ተስፋ ከማጨለም በትናንት ተነጋግሮ መተማመን የሚፈጠርበት ለወደፊቱም በመተማመንና በመከበባር በእኩልነት መኖር የሚስችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመስረት መትጋቱ ነው የሚበጅ፡፡ እንጅማ ወያኔ በሰጠን የመቶ አመት የቤት ስራ ባለፈ ነገር እየነታረኩ ከወያኔን አገዛዝ መላቀቅ የማይታሰብ ነው፡፡ ለመሆኑ የቱ ይቀድማል ያለፈው ሥርዓት በአያት አባቶቻችን ላይ አደረሰ የሚባለው ወይንስ የዛሬው ገዢ በእኛ ላይ የሚያደርሰው ፡፡

የዘር ዝናር የታጠቀ ሳይሆን ኢትጵያዊ ግርማ ሞገስ የተላበሰ፣በጠብ-መንጃ ሳይሆን በምርጫ ኮሮጆ ውጤት ለሥልጣን የበቃ በሕዝብ የታመነና በህዝብ የሚተማመን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት መመስረት ቢቻል ፤ ሀገራዊ መሰረቶችን ለማጽናት፤እኩልነትን ለማረጋገጥ፤አብሮነትን ለማጎልበት ወዘተ የሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ይመከርባቸዋል መልስ ይፈለግላቸዋል፤ በዚህም የታሪካችን መጥፎ ገጽታ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የልዩነት ምክንያት መሆኑ አንዲያበቃ በመተማመን ቤተ መዘክር እንዲቀመጥ መልካሙም እንዲጎለብት ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ለዛ የሚያበቃንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማግኘት ቀዳሚው አጀንዳ ቢሆንስ?

The post የመቶ አመቱ የቤት ስራ – ይገረም ዓለሙ appeared first on Zehabesha Amharic.

Source:: Zehabesha

No comments:

Post a Comment