Monday, October 19, 2015

የብአዴን የቀድሞ ታጋዮች መንገድ ላይ ወጥተው በመለመን ላይ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡


ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብአዴን የተመሰረተበትን 35ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ የተለያዩ ጋዜጠኞችንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ያካተተ ጉዞ ላይ ፣ የትግል ተሞክሮ እንዲያካፍሉ የተጋበዙት የቀድሞ ታጋዮች በርካታ ጓዶቻቸው መጠለያ በማጣት በየከተማው በላስቲክ ቤት መንገድ ላይ እንደሚኖሩ ለጎብኝዎች ተናግረዋል፡፡
‹‹ ህዝብ እንደኖረው ለመኖር ዕድሉን አልተሰጠንም፡፡ ›› የሚሉት ነባር ታጋዮች ገዥው መንግስት፣ድርጅታቸውም ሆነ በየአካባቢው የሚያገለግሉ ባለስልጣናት ” ኢትዮጵያን በክፉ ቀን ከአረመኔው አገዛዝ ያወጡ ፤ ጊዜያቸውንና አካላቸውን መስዋዕት ያደረጉ ናቸው በማለት ግምትና ዋጋ አልተሰጠንም ›› በማለት በለቅሶ ለጎብኝዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ገዥው መንግስትና የታገሉለት ድርጅት እንደረሳቸው በምሬት የሚናገሩት የቀድሞ ብአዴን ታጋዮች፣ ዛሬ መጠለያ በማጣት መንገድ ላይ በላስቲክ ቤት የወደቁ፣ የግለሰብ ቤት ዘበኛ የሆኑ፣ የግለሰብ ቤት እንጀራ ጋጋሪና ልብስ አጣቢ በመሆን የእለት እንጀራ ለማግኘት ደፋ ቀና የሚሉ መንገድ ላይ ቁጭ ብለው በሚያሳዝን ህይወት ውስጥ በልመና ላይ ያሉ የቀድሞ ታጋዮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
‹‹ ያሳለፍነው ህይወት ያሳደረብን ስነልቦናዊ ጉዳት ከባድ ነው፡፡ ›› የሚሉት የቀድሞ ታጋዮች፣ የታገሉለት ድርጅት በጉልበታቸው ተጠቅሞ የወረወራቸው ያህል እንደሚሰማቸው በምሬት በመናገር ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው የኑሮን ፈተና ለመቋቋም አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
የብአዴን መስራች ታጋዮች በትግሉ ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ በማደረግ የአካል ጉዳት ያገኛቸው፣ታላቅ የስነልቦና ችግር የደረሰባቸውና የጓዶቻቸውን ህይወት የተነጠቁ በመሆኑ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ በአሁኑሰዓት በወረደ የኑሮ ሁኔታ መኖራቸው እየታወቀድርጅታቸው የስልጣን መንበሩን ከታሰበው ዓመታት በላይ ከያዘ በኋላ ዘወር ብሎ አለማየቱን በሃዘን ይናገራሉ፡፡
የገቢ ምንጭም ሆነ ልጅ ሊያሳድጉበት የሚችሉበት መንገድ ሊፈልግላቸው እንደሚገባ የሚናገሩት ታጋዮች ፣ አብረው የታገሉት ጓዶች በተንደላቀቀ ህይወት ሲኖሩ እነርሱ በተጎሳቆለ ሁኔታ መገኘታቸውን ‹‹ የነዋሪዎች አኗኗሪ ነን ›› በማለት ይገልጹታል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ከፌደራልና ክልል የተሰባሰቡት ጋዜጠኞች፣የስነጥበብ ባለሙያዎችና የድርጅቱን ደጋፊ የማህበረሰብ አባላት ብአዴን ኢህአዲግ በሰራው ጀብድና ባሳለፈው የትግል ጉዞ ውጣ ውረድ ለመኩራራት ቢያስብም ፣ የጉዞው ዓላማ እንዳልተሳካለት በጉብኝቱ የተሳተፉት ባለሙያዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡አንዳንድ የጉብኝቱ አካላትም ጉብኝቱን አቋርጠው መሄዳቸውን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
ብአዴን ኢህአዴግ በልዩ ልዩ ሰበብ ለበዓላት የሚያዎጣውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በትግሉ ወቅት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለው ዛሬ የሰው እጅ በማየት ለሚኖሩት የቀድሞ ታጋዮች በትግሉ ወቅት ለተጎዱ አካባቢ ነዋሪዎች እንክብካቤ ሊያውለው ይገባ ነበር በማለት ጎብኝዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ድርጅቱ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ዜጎች በድርቁ ሳቢያ በምግብ እጥረት ፣ በውሃ ጥምና በተለያዩ ችግሮች እየተሰቃዩ ፣ ለ35ኛ አመት በአሉ መቶ ሚሊዮኖችን ለማውጣት ማሰቡም ፣ ብአዴንን እያስተቸው ነው።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment