• የኢኮኖሚ መዋቅሩ ከሳህራ በታች ከሚገኙ ሀገራትም ያነሰ ነው
• የወጪ ንግድ ገቢ እና የገቢ ንግድ ክፍተት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል
• ለውጭ ገበያ የቀረበው አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡና፣ ሰሊጥና የጥራጥሬ ሰብሎች መጠን በእቅዱ ከተያዘው በእጅጉ ያነሰ ነው
• ለውጭ ይቀርባል ተብሎ ከታቀደው ቡና የቀረበው ሩቡ ብቻ ነው
• መስራት የሚቻለውን ያህል የልማት ሥራ ሳይሰራ ቀርቷል
• ሥራ አጥነት በከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠር አካባቢዎችም ሰፊ ችግር ሆኗል
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ላለፉት 10 አመታት ኢትዮጵያ 11.2 በመቶ በማደግ በዓለም ፈጣን እድገት እያሳዩ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነችና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ጋር ልትመደብ እንደሆነ ሲናገር የነበረው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የኢኮኖሚ ውድቀት እንዳጋጠመው አመነ፡፡ የብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም የሁለተኛውን አምስት አመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (ከ2008-2012 ዓ.ም) ላይ ለመወያየት ያዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ እንደሚያሳየው በተለይም መንግስት ለኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር ነው የሚለው የግብርና ዘርፍ፣ የውጭ ንግድና የማኑፋክቼሪንግ ኢንዱስትሪው ውድቀት አጋጥሞታል፡፡
‹‹በአጠቃላይ በተጠናቀቀው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተመዘገበው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ከሚጠበቀው አንፃር ዝቅተኛ ነው፡፡ የኢኮኖሚው መዋቅር ለውጥ ከማረጋገጥ አንፃር የተመዘገበው አፈፃፀም ዝቅተኛ ነው፡፡›› ያለው ሰነዱ የኢኮኖሚ መዋቅሩ ከሳህራ በታች ከሚገኙ ሀገራትም ያነሰ እና በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አስምሮበታል፡፡ በኢኮኖሚው ችግር ምክንያትም ስራ አጥነት ከከተሞች አልፎ በገጠረ አካባቢዎችም ሰፊ ችግር እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ከሸቀጦች የወጪ ንግድ ይገኛል ተብሎ የተገመተው ገቢ በ2006 ዓ.ም ከነበረውም ያልተለየ፣ ከዚህ ገቢ የተገኘው የገቢ ንግድ (import) ወጪን የመሸፈን አቅሙም በ2007 ዓ.ም ከአለፈው ጊዜ ያነሰ ነው ያለው ሰነዱ፤ በወጪ ንግድ ገቢ (export) ወጪ እና በገቢ ንግድ ((import) ወጪ ያለው ክፍተትና ጉድለት እየሰፋ መጥቶ በ2007 ዓ.ም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡ የታየው ደካማ የውጭ ንግድ አፈፃፀም አስተማማኝ የውጭ ምንዛሬ በማግኘት ኢኮኖሚውን ለማሳደግ፣ ከውጭ ብድርና እርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ለሚደረገው ጥረት ማነቆ እንደሆነ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል፡፡
የውጭ ንግድ መዳከም የውጭ ምንዛሬ ለሚፈልጉትና አቀድኳቸው ላላቸው የመሰረተ ልማት፣ የኢንዱስትሪና የማህበራዊ ልማት እንዳይሳኩ እየፈጠረው ያለው እንቅፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል፡፡ ለውጭ ገቢ ንግድ መዳከም በዋነኛነት የማምረት አቅም አለማደግ፣ የማኑፋክቸሪንግና የግብርና ሸቀጦች በመጠን፣ በአይነትም፣ በጥራት ማምረት አለመቻሉ እንደሆነ በሰነዱ ላይ ተገልፆአል፡፡
በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መጨረሻ ለውጭ ገበያ ይቀርባል ተብሎ የነበረው ቡና ሩብ ያህሉን እንኳን ማቅረብ አልተቻለም ያለው ሰነዱ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ለውጭ ገበያ ይቀርባሉ ተብሎ የነበሩት የአበባ፣ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ምርቶችም በቡና ገበያ ላይ ከታየውም በላይ ክፍተት እንደነበረበት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ሰነዱም ‹‹በግብርና ዘርፍ የኤክስፖርት ሰብሎች የሆኑት አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቡና፣ ሰሊጥና የጥራጥሬ ሰብሎች ሲሆኑ ለውጭ ገበያ የቀረበው መጠን ይደረጋል ተብሎ ከታቀደው በእጅጉ ያነሰና በማኑካፍቼሪንግ ነባር ኢንዳስትሪዎችና በከፍተኛ አቅማቸውና በጥራት እንዲያመርቱ፣ በተጨማሪም አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በስፋትና በጥራት መልምሎ ወደ ሥራ ማስገባት በታቀደው ልክ ሊፈፀም ባለመቻሉ ለወጪ ንግድ የማምረት አቅማችን ዝቅተኛ መሆኑን ዋና ምክንያቶች ነበሩ›› ብሏል፡፡
መንግስት በታክስ አሰባሰብም ትልቅ ክፍተት እንዳለበት ያመነው ሰነዱ ‹‹ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት አማካይ አፈፃፀም ለመድረስ በታክስ አስተዳደርና አሰባሰብ ተጨማሪ ጥረት ማደረግ እንዳለብን ያመለክታል፡፡ መሰብሰብ የሚችለው የታክስ ገቢ አለመሰብሰቡ መስራት የሚቻለውን ያህል የልማት ሥራ በዛው ልክ ሳይሰራ ቀርቷል ማለት እንደሆ ከልብ ሊጤን ይገባዋል›› ብሏል፡፡
The post መንግስት ኢኮኖሚው ውድቀት ላይ መሆኑን አመነ appeared first on Zehabesha Amharic.
Source:: Zehabesha
No comments:
Post a Comment