መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የሆላንዱ ዴልታሬስ ኩባንያ ከፈረንሳዩ ቢአር ኤል አይ ኩባንያ ጋር በመሆን በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ጥናት እንዲያካሂድ በግብጽና በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተወክሎ ነበር። ይሁን እንጅ ጥናቱ ከመጀመሩ በፊት በምን መንገድ መካሄድ አለበት በሚለው ነጥብ ዙሪያ ከፈረንሳዩ ኩባንያ ጋር ሲነጋገሩ ቢቆዩም መስማማት አልቻሉም። ኩባንያው ከኢሳት ለቀረበለት የጽሁፍ ጥያቄ በሰጠው መልስ ” ጥናቱን በጥራትና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለማካሄድ እንደ ቅድመ ሁኔታ ብናሰቀምጥም፣ ሌላው ኩባንያ የሚቀበለው አልሆነም” ብሎአል። ዴልታሬስ ገለልተኛ ተቋም እንደመሆኑ ፣ ይህንን ውስብስብና ጠቃሚ ፕሮጀክት በጥራት ለማካሄድ ያሳየው ፍላጎት ተቀባይነት በማጣቱ ከስምምነቱ መውጣቱን ቢገልጽም፣ ውሳኔውን በተመለከተ እስካሁን ከሁለቱም መንግስታት መልስ እንደላገኘ ተናግሯል።
ዴልታሬስ የሰጠውን ውሳኔ በተመለከተ ሁለቱም አገራት እስካሁን በይፋ የተናገሩት ነገር የለም። ይሁን እንጅ በግብጽ የተመረጠው ዴልታሬስ ኩባንያ ያነሳው የገለልተኝነትና የጥራት ጥያቄ፣ ግብጾች በፈረንሳዩ ኩባንያ ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ የሚያደርጋቸው ነው። በኢትዮጵያ በኩል የተመረጠው የፈረንሳዩ ኩባንያ በሆላንዱ ኩባንያ ለቀረበው ጥያቄ በይፋ መልስ አልሰጠም፣ ጥናቱን እንደሚቀጥል ወይም እንደማይቀጥል አላስታወቀም።
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment