Wednesday, September 23, 2015

የጸረ ሙስና ኮምሽን ኮምሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን የባለሥልጣናትን ሐብት ምዝገባ መረጃ ለመገናኛ ብዙሃን ክፍት ለማድረግ ፍላጎት አለመኖሩን ተናገሩ


መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኮምሽነሩ ሰሞኑን በጽ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለጉዳዩ በሰጡት ማብራሪያ ከ95 ሺህ በላይ ተሿሚ፣
ተመራጮችና የመንግስት ሠራተኞች ሐብት ኮምሽኑ መመዝገቡን፣ እንዲሁም ከ14 ሺህ በላይ ሐብት አስመዝጋቢዎች የቤተሰቦቻቸውን ሐብት አሳውቀው ማስመዝገባቸውን አረጋግጠዋል፡፡ “ይህ መረጃ ለምን ይፋ አይደረግም» ለሚለው ጥያቄም ሲመልሱ ለመገናኛ ብዙሃን የመናገር ግዴታ እንደሌለባቸው በመግለጽ በግል መረጃ ለሚጠይቁ ሲሰጥ መቆየቱንና ይህ አሰራርም እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ኮምሽኑ በ2007 በጀት ዓመት ብቻ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ከኮምሽኑ አቃቤ ሕግ በተጠየቀው መሰረት 137 የሃብት አስመዝጋቢ መረጃዎችን በጹሑፍ መልስ መስጠቱን ገልጿል፡፡
ኮምሽኑ በምዝገባ ወቅት እያንዳንዱ ምዝገባው የሚመለከተው አካል ሐብትና ንብረቱን ሳይደብቅ ማስመዝገቡን በትክክል ማረጋገጥ የሚችለው ተመዝጋቢው አምኖ የሰጠው መረጃ ለሕዝብ ደርሶ ከሕዝብ በሚመጣ መረጃ መሰረት ቢሆንም፣ ኮምሽኑ መረጃውን በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለሕዝብ ለመግለጽ ፈቃደኛ አለመሆኑ መግለጹ ምዝገባውን ፋይዳ ቢስ እንዳደረገው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አስተያየታቸውን እየሰጡበት ይገኛሉ፡፡
የኢህአዴግ አብዛኛዎቹ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በቀበሌ፣ በወረዳና በክፍለከተሞች አካባቢ የሚገኙ ትናንሽ ተሿሚዎች በሙስና በመዘፈቅ ከገቢያቸው በላይ እንደሚኖሩ የሚታወቅ ሲሆን ፣ ኮምሽኑ መረጃ ለመከልከል ገዥው ፓርቲ እስከአንገቱ የተዘፈቀበትን የሙስና ቅሌት ለመሸፋፈን የታለመ ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
ኮምሽኑ ከዚህ ቀደም የባለስልጣናት ሐብት ምዝገባ መረጃን ይፋ የማያደርገው መረጃውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውቶሜት የማድረግ ስራ ባለመጠናቀቁ መሆኑንና ስራው ሲጠናቀቅ በድረገጽ አማካይነት መረጃው ይፋ ይሆናል የሚል ምክንያት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ “የባለስልጣናትን የሃብት መጠን የማሳወቅ ግዴታ የለብኝም “፣ በሚል ኮሚሽኑ የሚያቀርበው አዲስ ምክንያት ቀድም ብሎም ይህ ነው የሚባል ህዝባዊ አመኔታን የሌለውን ተቋም ይበልጥ የሚገድለውና ለሙስናና መስፋፋት አዲስ በር የሚከፍት መሆኑን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን አስተያየት ሰጪዎችን ጠቅሶ የላከው ሪፖርት ያብራራል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment