መስከረም ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ከተማ በየካቲት ወር 2008 ጀምሮ ይከናወናል ተብሎ የታቀደው የፈጣን አውቶቡስ መስመር ግንባታ
ፕሮጀክት ከአዋጪነት አንጻር በሚገባ በጥናት ያልታየና በአሁኑ ሰዓት የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን የሚያሳጣ ነው በሚል ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ነዋሪዎች እንደጠቆሙት ፕሮጀክቱ ከዊንጌት፣ በጎፋ ገብርኤል አድርጎ ወደ ጀሞ የሚዘልቅ ለከተማ አውቶቡስ ብቻ የተከለለ መስመር ለመገንባት የታቀደ ሲሆን ፣ ይህ ፕሮጀክት በጠቅላላው 60 ሚሊየን ዩሮ
ይፈጃል ተብሎ ይገመታል፡፡ ፕሮጀክቱ በየካቲት ወር 2008 ተጀምሮ በ15 ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዷል። ለዚህ ግንባታ የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ 50 ሚሊየን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምቶአል፡፡
ፕሮጀክቱ የሕዝብ የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ ያስችላል በሚል የታቀደ ይሁን እንጂ ከአዋጪነት አንጻር ተገቢው ጥናት አልተካሄደበትም ያሉት ምንጮቹ ፣ ይህን መስመር ከመገንባት በርካታ አውቶቡሶችን በማሰማራት የትራንስፖርት ችግርን መቅረፍ ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ አለመደረጉ አሳሳቢ መሆኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቱ በዝርዝር የኢንጂነሪንግ ጥናት ላይ የሚገኝ ሲሆን የአውቶቡስ መስመሩን ለመዘርጋት በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የመንገድ፣ የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌ መሰረተ ልማቶችን እንዲሁም በርካታ ሕንጻዎችን የሚያፈራርስ ሲሆን በዚህም ምክንያት በመስመሩ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ከህዝብ ጋር ሳይወያይ ወደትግበራ መግባቱ ነዋሪዎቹን ያበሳጨ ሲሆን፣ ብድር ተገኘ ተብሎ ዝም ብሎ ወደቁፋሮ መግባት መንግስታዊ ሌብነትን ከማስፋፋት የዘለለ ትርፍ አያስገኝም ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡
Source:: Ethsat
No comments:
Post a Comment