Friday, July 3, 2015

የጦር መሳሪያቸውን ያስመዘገቡ ሰዎች አስገዳጅ መመሪያ ተላለፈባቸው


ሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ የኢህአዴግ መንግስት የግል የጦር መሳሪያ የያዙ ዜጎች ህጋዊ ፈቃድ ከመንግስት በመውሰድ፣ የጦር መሳሪያቸውን እንደንብረት እንዲይዙ አዲስ መመሪያ በማውጣት፣ በተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች መሳሪያዎቻቸውን እያስመዘገቡ ፈቃድ ውሰደዋል። ይሁን እንጅ ገንዘብ እየከፈሉ ፈቃድ የወሰዱ ባለንብረቶች፣ በራሳቸው ገንዘብ የገዙትን መሳሪያ መሸጥ፣ መለወጥ ወይም ለሌላ ሰው ማውረስ እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል። መሳሪያውን የሸጠ፣ ያወረሰ ወይም የጠፋበት ሰው ሙሉውን የመሳሪያ ዋጋ በጥሬ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ማድረግ እንዳለበት መመሪያው ያስገድዳል።
የጦር መሳሪያ ያስመዘገቡ ሰዎች በ1 ለ10 እንዲደራጁ የተገደዱ ሲሆን፣ ከመካከላቸው አንዱ ቢተኩስ ወይም መሳሪያውን ቢሸጥ ሌሎች ተከታትለው ለሰብሳቢያቸው ሪፖርት ማድረግ አለባቸው። ሰብሳቢውም መረጃውን ለአካባቢው የመንግስት ተጠሪ ሪፖርት ያደርጋል።
መሳሪያቸውን ተገደው ያስመዘገቡ ሰዎች አሰራሩን እየተቃወሙት ነው። ገንዘብ አውጥተን ከገዛን በሁዋላ መሸጥ መለወጥ ወይም ማውረስ አትችሉም መባላችን፣ ከዚህም በላይ በተለያዩ ምክንያቶች ብንተኩስ ትጠየቃላችሁ መባላችን አግባብ አይደለም ይላሉ።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የመከላከያ ሰራዊት አባላት የጦር መሳሪያዎቻቸውን እየሸጡ እንደሚጠፉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከላሽንኮቭ የሚባለው መሳሪያ እንደ ይዞታው እስከ 60 ሺ ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። አንዳንድ የአካባቢ የጸጥታ ሹሞችም የጦር መሳሪያዎችን በመነገድ ከፍተኛ ሃብት እያፈሩ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

No comments:

Post a Comment