Thursday, August 13, 2015

የህወሃት አመራሮች በዲሲከደጋፊዎች ጋር ውይይት አደረጉ


ኢሳት ዜና (ነሐሴ 7, 2007 ዓም)
በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት መቋጫ እንዳላገኘ በሚገለጽበት በአሁኑ ወቅት የህወሃት አመራሮች በዋሽንግተን ዲሲ ከትግራይ ተወላጆች ጋር ተወያይተዋል። ባለፈው እሁድ ለትግራይ ተወላጆች ብቻ በሚል በተደረገው ጥሪ መሰረት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተካሄደው ስብሰባ የመሩት ከኢትዮጵያ የመጡት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማሪያምና አቶ ዳንኤል አሰፋ የተባሉ የህወሃት አመራር አባላት መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።
ቁጥሩ አንድ መቶ ያህል ሰው የተገኘበት ስብሰባ የመሩት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማሪያምና አቶ ዳንኤል አሰፋ፣ የትግራይ ክልል ካቢኔ አባላት መሆናቸውን ለተሰብሳዊው ገልጸው፣ ወደ አሜሪካ የመጡት በሲያትል ለተከበረው 41ኛ የትግራይ አመታዊ ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት እንደሆነ በማስረዳት መድረኩን ለውይይት ከፍተዋል።
በትግራይ በተለያዩ መስኮች አሉ የተባሉ ችግሮች የተነሱባቸው የመድረክ መሪዎች፣ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ትግራይም በአጠቃላይ ኢትዮጵያም በተስፋ ጎዳና ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። “በቀረጽነው በሳል ፖሊሲ በሃገሪቱ መረጋጋት አስፍነናል፣” ሲሉ ለተሰብሳቢው ገልጸዋል።
በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጥ ስለነበረውና ስለቀጠለው ልዩነትም ከተሰብሳቢው ጥያቄ መቅረቡ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። “እናንተ ለትግራይ ህዝብ ምንም አልሰራችሁም” በማለት በወቀሳ የጀመሩት አንድ ተሰብሳቢ፣ “አማራጭ አጥተን እናንተን እየደገፍን ለመቀጠል ተገደናል፣ ከእናነተ ውጭ ያለው አማራጭ ጉድጓድ ስለሆነና፣ የትናንቶቹ ተመልሰው እንዳይመጡ ከእነቸግራችሁ ከእናንተ ጋር ቆመናል” በማለት በተቃውሞ ጎራ ያለውን ወገን በጥልቅ ጉድጓድ መስለዋል፥ ጠንካራ ህወሃት ስለሚያስፈልግ አንድ ሆነው እንዲቆሙ ተማፅነዋል።
በራያ ቢራ ፋብሪካና በተለያዩ የንግድ መስኮች የሚሳተፉ አቶ ዳዊት ገ/እግዚሃብሄር የተባሉ የትግራይ ተወላጅ፣ በህወሃት መሪዎች በተለይም በትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች ላይ ያነሱትን ቅሬታና ተቃውሞ በተመለከተ የተለያዩ ተሰብሳቢዎች ማብራሪያ የጠየቁ ቢሆንም፣ ቀጥተኛና አጥጋቢ ምላሽ ከመድረክ አለመሰጠቱን በድምጽ ተደግፎ ለኢሳት የደረሰው ዜና ያስረዳል።
ባለሃብቱ ጥያቄያቸው ግልጽ እንዳልሆነ የገለጹት በመንግስት ፖሊሲ ተጠቃሚና አትራፊ መሆናቸውን በመግለጽ ዝርዝር ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋል። የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ እያለ “የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ብሄር ብሄረሰቦች ለምንድነው የሚጠሉን?” በማለት ለህወሃት ባለስልጣናት ጥያቄ ያቀረበው ተሰብሳቢ፣ “ዲሞክራሲና አንድነትን የማንፈልግ የሚመስላቸው ለምንድን ነው?” በማለት ጥያቄያቸው አጠቃለዋል።
የመድረክ መሪዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አይጠላንም የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ይልቁንም ባለን ቦታና ሚና ይበልጥ እየተከበርን እንገኛለን የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል የትግራይ ተወላጆች በሰላምና ተከብረው እንደሚኖሩ አስረድተዋል። የሚጠሉን ተቃዋሚዎችና ከህወሃት ያፈነገጡ ግለሰቦች ናቸው የሚል ማላሽ ሰጥተዋል።
በአዲስ አበባ ደረጃ ልማቱ ለምን በትግራይ አይካሄድም የሚል ጥያቄ የተነሳ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ አመታዊ ስፖርት ውድድር ባህርዳር ከመሄድ ይልቅ መቀሌ ውስጥ ለምን ትልቅ ስታዲየም አልተሰራም የሚል ጥያቄ ከተሰብሳቢዎች ተነስቷል።
ከኤርትራ መንግስት ጋር ስላለው ሁኔታ በተለይም ከድንበር አካባቢ የትግራይ ተወላጆች እየተመረጡ ወታደራዊ ስልጠና ስለመውሰዳቸው ተጠይቀዋል።
የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንትና የህወሃት ሊቀመንበር የአቶ አባይ ወልዱ ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማሪያም የኢትዮጵያ ደህንነት መስሪያ ቤት ዋና ሃላፊ የአቶ ጌታቸው አሰፋ ወንድም የሆኑት የአቶ ዳንኤል አሰፋ ስብሰባውን ሲያጠቃልሉ በጥቂት ሰዎች አጀብ ኩዊን ሼቫ ወደተባለው ምግብ ቤት በማምራት፣ ከጥቂቶቹ ጋር የተናጥል ውይይት ማድረጋቸውን መረዳት ተችሏል።
Source :http://ethsat.com/amharic/

No comments:

Post a Comment