Friday, March 20, 2015

ለብአዴን አባላት ……ከሰማችሁ …….ከሞግዚት አስተዳደር ተፋቱ! – አንበርብር ከአማራ ሳይንት



tplf
አፄ ዮሃንስ ንጉስ ተከለ ጊዮርጊስን ድል ነስተዉ ጎጃም ሲገቡ ራስ አዳል አልተደሰቱባቸዉም ነበርና ራስ አዳል ሸሽተዉ በርሃ ገቡ፡፡ አፄዉ ለራስ ደስታ ተድላ ዘመዳቸዉን ድረዉ በጎጃም ላይ ይሾሟቸዋል፡፡ ሆኖም ግን አፄ ዮሃንስ በራስ ደስታ ተድላ ላይ ሙሉ እምነት አልነበራቸዉምና በስራቸዉ ሐጎስ የሚባል አስተዳዳሪ ሾመዋል፡፡ ራስ አዳል ግብር በዛብን ያለዉን ህዝብ አስተባብረዉ የአፄ ዮሃንስ ሰራዊት ሲያጠቁ በዉጊያዉ አፄዉ የሾሟቸዉ ራስ ደስታ እና ሞግዚቱ ሐጎስ ይገደላሉ፡፡
የሟቾችን አስክሬን ወደቀብር ሲወጣ የራስ ደስታን በእንጨት አልጋ፤ የሐጎስን በአጎበር በተከለለ አልጋ ሲወሰዱ ባለቅኔዉ የጎጃም ህዝብ
“እኔስ ምን ቸገረኝ ካንተ አልዋጋ
እስራኤሉን በእንጨት ወታደሩን ባልጋ”
እያለ ሲቀኝ እንደነበር እና የሞግዚት አስተዳደር መጨረሻዉ ዉርድት እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡(ምንጭ፡- የንግስና ሥርዓት እና የነገስታት የዘር ሃረግ፤በጥላሁን ብርሃነ ስላሴ)
የሞግዚትነት አስተዳደር ሙሉ አስተዳደር አይደለም፡፡ የይስሙላ አስተዳደር ነዉ፡፡ ሲፈለግ የሚፀና ሳይፈለግ የሚነሳ፣ ያልፀና እና መልካም ፈቃድን ያልተከተለ አሰራር ነዉ፡፡ የሞግዚትነት አስተዳደር ህዝብን ካለማመን የሚነሳ ቢሆንም ዋና ዓላማዉ የራስን የበላይነት ጠብቆ ማቆያ ነዉ፡፡
አፄ ዮሃንስ ጎጃሜዉንና ሆነ ራስ ደስታን ስላላመኗቸዉ፣ የሐጎስ ሞግዚትነት አስፈልጓቸዋል፡፡ የሞግዚት አስተዳዳሪነት ህዝብን ካለማመን እና ከመጠራጠር መጥቶ በመጨረሻዉ ሰዓት ክብር የሚሰጠዉ ለሞግዚቱ ነዉ፡፡
ሕወሓት-ኢህአዴግ በየቦታዉ ከሚሾማቸዉ አስተዳደሪዎች ጀርባ አንድ ሞግዚት እንደሚያስቀምጥ ትንሽ እልፍ ወይም ገባ ብሎ ለመመረመረ ከነደስታ ጀርባ ሺህ ሐጎሶችን መመልከት ይችላል፡፡ በሞግዚት አስተዳደር ስር መዉደቅ ሁለት ጊዜ መሞት ነዉ፡፡ አንድ ጊዜ ተንቆ እየተደገፉ መኖር እና ነፃነትን ማጣት ሲሆን ሁለተኛዉ በህዝቡም ሆነ በገዥወቻችሁ ፊት ታማኝነት ማጣት እና በስተመጨረሻ የራስ ደስታን ዕጣ መጋራት ነዉ፡፡
የብአዴን ሰዎች እኔ ከማዉቃችሁ ሰዎች ጨምሮ ኑሯችሁ የቀንድ አዉጣ፣ አስተዳደራችሁ የሞግዚት አስተዳደር እና ከሁለት ያጣ ወገን የሆናችሁ ናችሁ፡፡ በቅርብ እየሰማነዉ እንዳለሁ ጀርባችሁ ሲፋቅ ግንቦት 7 እየተባላችሁ፣ ታማኝነታችሁን አጥታችኋል፡፡ በእነ ሓዱሽ እየገፋችሁት ያለዉ የሞግዚት አስተዳደራችሁ ወደ ሞት የሚወስዳችሁ ከመሆኑ በላይ እናንተን በእንጨት ሞግዚታችሁን በወርቅ ሲጭኗችሁ ሁለተኘዉ ሞት ነዉ፡፡
ጊዜዉ ወደ ወገን የመጠቅለያ ነዉ፡፡ ያረጁትን የብአዴን መሪዎቻችሁን እርሷቸዉ እና ከአዲሱ የአማራዉ ክልል ትዉልድ ጋር ስለህዝባችሁ ተነጋሩ፡፡ በመንግስት ላይ አሻጥር እየሰሩ ስልጣን የያዘዉን አካል ማንኮታኮት እና ማዉረድ ከእናንተ ይጠበቃል፡፡ እኔ የማምናቸዉ ብአዴን ዉስጥ ሰርገዉ የገቡ የቅርብ ሰዎች አሉኝ፡፡ ድርጅቱን በብዙ ነገር እየበከሉት ቀፎዉን ሲያስቀሩትእያየሁ ብዙ ጊዜ አብረን የድርጅቱን መፍረሻ ቀን ቆጥረናል፡፡ አሁንም አስተሳሰብ ለዉጥ ላይ እያተኮርን በየመስሪያ ቤቱ ብአዴን በሚያካሂደዉ አደረጃጀት እና ስብሰባ እየገባን ሌሎችን በአስተሳሰብ ነፃ እያወጣን ጎድጓዱን አርቀን መቆፈር እንችላለን፡፡
እንደ መዉጫ የሞግዚት አስተዳደርነት መነሻዉ ህዝብን መናቅ እና አለማመን ስለሆነ እንደ ራስ ደስታ ሁለተኛ ሞት ሳንሞት ራሳችን ከሞግዚትና ከአሳዳሪዎቻችን ነፃ እናድርግ፡፡ የብአዴን አባሎች ሕወሓት በተደጋጋሚ ጀርባቸዉን ሲፍቀዉ ግንቦት 7 ናቸዉ እያላችሁ ሳትታመኑ አብራችሁ ልትኖሩ አይገባም፡፡ ከድርጅቱ በአስተሳሰብ በልጣችሁ ሄዳችሁም አልሄዳችሁም ከመጠርጠር እና ካለመታመን ስለማትድኑ ዛሬዉን ከሞግዚት አስተዳደር ራሳችሁን አላቃችሁ ተከተሉን፡፡
source: zehabesha.com

No comments:

Post a Comment