Tuesday, November 8, 2016

በአዲስ አበባ ሁለት ግብጻውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ


ኢሳት (ጥቅምት 29 ፥ 2009)
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደርጉ ሁለት ግብጻውያን ባልታወቀ ምክንያት ከቀናት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
በጸጥታ ሃይሎች ለእስር ከተዳረጉት ሁለት ግብጻውያን መካከል አንደኛው ካዛንቺስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የራዲሰን ብሉ ሆቴል ረዳት ዋና ስራ አስፈጻሚ መሆናቸውን በሃገር ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች ዘግበዋል።
ከአራት አመት በፊት ግብፅ ከሚገኘው ተመሳሳይ ሆቴል ወደ ኢትዮጵያ ተዛውረዋል የተባሉ ታሃ-ማንሱር በስራ ላይ እያሉ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሳምንታዊ ካፒታል ጋዜጣ አስነብቧል።
ሁለተኛው ግብጻዊ ግን የሚሰራበት ድርጅትም ሆነ ማንነቱ ያልታወቀ ሲሆን፣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በቀጣዩ ቀናቶችን ዝርዝር መረጃን ለመስጠት እንደሚጠበቅ ለመረዳት ተችሏል።
ይሁንና በአዲስ አበባ የሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ ምናሽን ከመስጠት ተቆጥቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለአንድ አመት ያህል ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ ከቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ ግብፅ አስተዋጽዖ አድርጋለች ሲል ቅሬታን ማቅረቡ ይታወሳል።
የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው ሃገራቸው በውጭ ሃገር ጉዳይ ጣልቃ አልገባችም በማለት ያቀረበችውን ቅሬታ አስተባብለዋል።
ሁለቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግብጻውያን በምን ጉዳይ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እስከ አሁን ድረስ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የቤት ለቤት ፍተሻን ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል። ለሁለት ሳምንት ያህል በተካሄደው በዚሁ ዘመቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ተነግሯል።
ይሁንና መንግስት ለእስር የዳረጋቸውን ሰዎች ቁጥርና ማንነት ከመግለጽ የተቆጠበ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸው ለእስር የተዳረጉባቸው ሰዎች በበኩላቸው በድርጊቱ ስጋት እንደሆነባቸው ይገልጻሉ።
የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳም ሹክሪ በሁለቱ ግብጻውያን ጉዳይ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በአዲስ አበባ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሊቢያ ጉዳይ ላይ በሚመክር አህጉራዊ ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሚኒስትሩ በሁለቱ ሃገራት መካከል ስላለ አለመግባባት እንዲሁም ለእስር ስለተዳረጉ ሁለት ግብጻውያን ውይይትን ያካሄዳሉ መባሉን የግብፅ መገናኘ ብዙሃን ዘግቧል።

Source: http://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8B%B2%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A3-%E1%88%81%E1%88%88%E1%89%B5-%E1%8C%8D%E1%89%A5%E1%8C%BB%E1%8B%8D%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%89%81%E1%8C%A5%E1%8C%A5%E1%88%AD/

No comments:

Post a Comment