Saturday, December 26, 2015

እነ ጌታቸው ሺፈራው 28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተሰጠባቸው


በሽብር ተጠርጥረው መያዛቸውን መርማሪያቸው ተናግሯል
‹‹ካሁን በፊት ይዝቱብኝ ነበር፤ ጋዜጠኛ በመሆኔ ነው የታሰርኩት›› ጌታቸው ሺፈራ
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ትናንት ታህሳስ 15/2008 ዓ.ም በያሉበት ታድነው የታሰሩት ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው፣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ዳንኤል ተስፋየ እና ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል ዛሬ ታህሳስ 16/2008 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት ቀርበው 28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በሽብር ተጠርጥረው መታሰራቸውን በመግለጽ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ፖሊስ ታሳሪዎቹ የተጠረጠሩበትን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪዎች ‹‹የአርበኞች ግንቦት 7 አባል በመሆን፣ በመመልመል፣ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ግንኙነት በመፍጠር የሽብር ወንጀል ሊፈጽሙ ሲሉ ተይዘዋል›› ብሏል፡፡
ተጠርጣሪዎች ስለተጠረጠሩበት ወንጀል እና ስለተጠየቀባቸው የጊዜ ቀጠሮ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ‹‹ካሁን በፊት በተደጋጋሚ ይዝቱብኝ ነበር፤ እኔ ጋዜጠኛ በመሆኔ ነው የተያዝኩት፡፡ ቤቴ ሲፈተሽ የተገኘውም የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች (ሰማያዊና መድረክ) መግለጫዎችና ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ከተባለው ወንጀል ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም፤ በነጻ ልሰናበት ይገባል›› ሲል ተናግሯል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ አባሉ አቶ ዳንኤል ተስፋየ በበኩሉ ‹‹በፍተሻ የተያዙብኝ ባንዲራ፣ ሲዲ እና ስልክ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለምርመራ የተጠየቀውን ያህል ጊዜ መፈቀድ የለበትም፤ አጭር ቀጠሮ ይሰጠን›› ሲል ጠይቋል፡፡
ሦስተኛው ተጠርጣሪ አቶ ሸዋታጠቅ ኃ/መስቀል ደግሞ ‹‹እኔ በቂርቆስ ክ/ከተማ በኢህአዴግ ተደራጅቼ የምሰራ ሰው ነኝ፡፡ ፖሊስ ከገለጸው ድርጅት ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም፤ ድርጅቱን ጭራሽ አላውቀውም፤ የልጅ አባት ስለሆንኩ አጭር ቀጠሮ ይሰጠኝ›› በማለት አመልክቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ግን ፖሊስ የጠየቀውን 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለጥር 14/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ከሁለት ወራት በፊት ከአርባምንጭ ተይዘው ወደማዕከላዊ የመጡት በአርባምንጭ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት እነ ሉሉ መሰለ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው 28 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ትናንት ለእስር ከተዳረጉት መካከል የሆኑት የሰማያዊ ፓርቲ አባላት አቶ ኤርሚያስ ጸጋየ፣ አቶ ፍሬው ተክሌ እና አቶ ቴዎድሮስ አስፋው ዛሬ ከሰዓት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
Source:https://t.co/q5WcPGIrlD

No comments:

Post a Comment