Thursday, October 22, 2015

ብአዴን ለበአል ማክበሪያ በሚል ህዝቡን በመዋጮ እያስጨነቀው ነው


ጥቅምት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-35ኛ አመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ ያለው ብአዴን ፣ በአማራ ክልል የሚኖረው ህዝብ ለበአሉ ማድመቂያ ገንዘብ እንዲያዋጣ እያስገደደ ነው። ነጋዴዎች ከብአዴን ጽ/ቤት የተጣለባቸውን ክፍያ ያለፍላጎታቸው በግድ እንዲከፍሉ ታዘዋል።
ከፍተኛ የረሃብ አደጋ በክልሉ ባንዣበበት በዚህ ወቅት፣ ብአዴን እንደ ህወሃትና ኦህዴድ መቶ ሚሊዮኖችን አፍስሶ በአሉን ለማክበር መሞከሩ ፣ ከታሪክ አለመማሩን ያሳያል የሚሉት አንድ በክልሉ የሚኖሩ መምህር፣ ድርጅቱን በህወሃት ተለጣፊነቱም ይከሱታል።
የክልሉ ህዝብ በኑሮ ውድነት የተነሳ በነፍስ ግቢ ነፍስ ውጪ ውስጥ ነው የሚሉት መምህሩ፣ ብአዴን ህዝቡን ሊደጉም ሲገባ፣ በተቃራኒው ህዝቡ ብአዴንን እንዲደጉም መገደዱ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው ይላሉ።
ብአዴን ከህወሃት ጋር በሽርክና ከያዛቸው የንግድ ድርጅቶች ማለትም ዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣አምባሰል የንግድ ሥራዎች፣ጥቁር አባይ ትራንሰፖርት ፣ ዘለቀ እርሻ ሜካናዜሽን ኩባንያዎች፣ ዳሽን ቢራ ቁጥር ፣ ጣና ፐልፕና ወረቀት ፋብሪካ ፣ ጎንደር ብቅል ፋብሪካ፣ ጣና ኮምዩኒኬሽን ፣ ሎያል ጥረት የጥጥ መዳማጫ ፋብሪካ ፣ በለሳ ሎጅስቲክሰ ፣ዋልያ ቆርኪ ፋብሪካ ፣ ተክራርዋ ፕላስቲክ ፋብሪካ ፣ ወልድያ አትክልትና ፍራፍ ፣ ትዛ የወተት ሃብት ፣ አዚላ የፍሪጅ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ፣ ጥቁር አባይ የመኪና መገጣጠሚ ፋብሪካ ፣ ቢዲሲ ኮንስትራክሽን ፣ ማዕድ የምግብ ኮምፕሌከሰ ፣ ቲቲ ኢንጅነሪንግ ፣ የጁ ማር እና ሌሎች 16 ድርጅቶች እንዲሁም ብአዴን ሼር የገባባቸው አባይ ባንክ፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ፣ ሬዲዮ ፋና እና ወጋገን ባንኮች በእያመቱ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ ቢያገኝም፣ የድርጅቱ ገቢ ለአማራው ህዝብ ምንም የፈየደለት ነገር የለም።
ምንጮች እንደሚሉት የብአዴን ጥረት የሚባለውን ተቋም የአንድ አካባቢ ሰዎች በመንደር ተሰባስበዉ ሀብቱን እንዳሻቸዉ የሚመዘብሩት ተቋም ነው።
በአላስፈላጊ የዉጭ አገር ጉዞ፡ የጥረት እና የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣኖችን እስከ ቤተሰቦቻቸው ውጭ አገር ልኮ ለማሳከም፣ የፖለቲካ ታማኞችን ለመግዛት የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ፣ ባለስልጣኖች በግለሰቦች ስም አክሲዮን በመግባት የሚያጋብሱት ከፍተኛ ገንዘብ ከብአዴኑ ጥረት የሚመጣ መሆኑን ምንጮች ይገልጻሉ።
ድርጅቱ ከ36 በላይ በሚሆኑት የንግድ ድርጀቶቹ በአሉን ማክበር እያቻለ ደሃውን ህዝብ ገንዘብ አዋጡ እያሉ ማስጨነቅ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው በማለት መናገራቸውን ዘጋቢያችን ከባህርዳር የላከልን ዘገባ ያመለክታል።
Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment