Friday, September 25, 2015

የአሜሪካ ኤምባሲ የኢትዮጵያን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ማስረጃ (TVET) እንደ ትምህርት ማስረጃ እንደማይቀበለው ገለጸ


መስከረም ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኤምባሲው የ2015 የዲቪ ሎተሪ የመጨረሻ ቀን ረቡዕ መስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም. መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን የቴክኒክና ሙያ የትምህርት ማስረጃን እንደሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ማስረጃነት ከዚህ ቀደም ሲቀበል መቆየቱን በማስታወስ ከአሁን በኃላ የማይቀበል መሆኑን አስታውቆአል፡፡
ኤምባሲው ይህን ለምን እንዳደረገ በመግለጫው የጠቀሰው ነገር ባይኖርም የኤምባሲው ምንጮች እንደጠቆሙት የአሜሪካ መንግስት የትምህርት መስፈርት ለውጥ ሊያደርግ የተገደደው በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እያሽቆለቆለ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የአሜሪካንን ስታንዳርድ የሚጠብቅ ባለመሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በቴክኒክና ሙያ የሰለጠኑ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የ2015 የዲቪ ዕድለኞች ወደአሜሪካ መግባት አይችሉም፡፡
ኤምባሲው በዚሁ መግለጫው የ2015 የዲቪ ሎተሪ ሒደት ማከናወኛ ጊዜ የፊታችን መስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅጠቁሞ ፣ ዕድኞች እስከ አሁን ድረስ ከአሜሪካን ኤምባሲ ጥሪ ካልደረሳቸው ለ2015 የዲቪ ሎተሪ አለመመረጣቸውን እንዲያውቁ ብሎአል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ እስከ ረቡዕ መስከረም 19 ቀን 2008 ድረስም ኤምባሲዉ ምንም አይነት አዲስ ጥሪ እንደማያካሂድም አስታውቆአል፡፡ በሚመጡት ጥቂት ቀናት ዉስጥ ቀጠሮ የተሰጣቸው ዕድለኞች የትምህርት መስፈርት ለዉጥ እንዳለ እንዲያውቁና በሥራ ልምድ መወዳደር ከፈለጉ አመልካቾች ለዲቪ ሎተሪ ፕሮግራም ማመልከቻ ብቁ የሚያደርጉትን የሥራ ልምዶች ከነዝርዝር መረጃዎቻቸዉ በኤምባሲዉ ድረ-ገፅ ላይ አስቀድመዉ እንዲመለከቱም አሳስቦአል፡፡
የ2017 የዲቪ ሎተሪ ምዝገባን የተመለከተ መረጃ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንም ኤምባሲው አስታውቆአል፡፡ በዲቪ 2015 ወደ 4ሺህ 988 ያህል ኢትዮጵያዊያንን እጣው ወጥቶላቸዋል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment