Tuesday, September 22, 2015

መንግስታዊ ተቋማት ሙስና በመፈጸማቸው ምርመራ ሊደረግባቸው ነው


ኢሳት ዜና (መስከረም 11፣ 2008)
የኢትዮጵያ የሐገር መከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ በ23 መንግስታዊ ተቋማት ላይ ምርመራ በመካሄድ ላይ መሆኑ ተገለጸ። የፌደራል የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱለይማን ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቲር ህግን ባልተከተለ መንገድ የ 2 ሚሊየን ዶላር ግዢ መፈጸሙን አመልክተዋል ።
በዚህ የሀገሪቱ ወታደራዊ ተቋም ህግን ባልተከተለ መንገድ ተፈጸመ የተባለውን ግዢ በተመለከተ ምርመራ መጀመሩን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለሰራዊቱና ቤተሰቡ በአነስተኛ ዋጋ እንዲከፈል የተዘጋጀ ስኳር ለነጋዴዎች በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ መኮንኖች መከሰሳቸውን ተመልክቷል። ተከሰሱ የተባሉት መኮንኖች ለግል ጥቅማቸው አውለውታል የተባለው 2.2 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ስለመታሰር አለመታሰራቸው የተባለ ነገር የለም።
የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱለይማን በሰጡት መግለጫ ከመከላከያ ሚኒስቴር በተጨማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ ሙስና የተፈጸመባቸው ድርጅቶች መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ የጸረ ሙስና ኮሚሽን በተለይ በሀገር መከላከያ ሚኒስተር ላይ ትኩረት በማድረግ የሰጠው መግለጫ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ሲሆን አንዳንድ ተመልካቾች ጉዳዩን ከህወሀት ክፍፍል ጋር አያይዘውታል።

No comments:

Post a Comment