Wednesday, August 26, 2015

በአቶ ማሙሸት አማረ የሀሰትና የተጠና ክስ መቅረቡን ጠበቃው ተናገሩ


ነኅሴ ፳ (ሀያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ ህዝብን አነሳስቷል በሚል ክስ የተመሰረተበት አቶ ማሙሸት አማረ ነሃሴ 20/2007 ዓ.ም አራዳ ምድብ ችሎት ቀርቦ ክሱን ተከታትቷል።
ከአራቱ ምስክሮች መካከል ሶስቱ ‹‹አቶ ማሙሸት አማረ 300 ብር ከፍሎ ሰልፍ እንድንወጣ አድርጎናል›› ሲሉ መስክረዋል፡፡
ይሁንና ምስክሮቹ ከማሙሸት ጋር በተገናኙበት ወቅት እንዲሁም ገንዘቡ ሲሰጣቸው፣ ሰልፉ ያለፈባቸውን ቦታዎችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ሲጠየቁ ‹‹አላስታውሰውም›› ከማለት ባለፈ ዝርዝር የምስክርነት ቃል ሳይሰጡ መቅረታቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል። ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ አቶ ማሙሸትን ያስያዙት ደህንነቶች መሆናቸውን አቶ ማሙሸትና ጠበቃው በችሎቱ የገለፁ ሲሆን፣ ምስክሮቹ በበኩላቸው ስራቸውን ሲጠየቁ ‹‹የግል›› እያሉ ከመመለስ ውጭ የመንግስት ስራ እንደማይሰሩ ተናግረዋል፡፡ ከሶስቱ ምስክሮች መካከል አንደኛው ስራውን ሲጠየቅ ‹‹የግል›› ብሎ የነበር ቢሆንም፣ በመስቀለኛ ጥያቄ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ጥቃቅንና አነስተኛ አመራር መሆኑን አምኗል፡፡
ከምስክሮቹ መካከል ሁለቱ የመኢአድ ደጋፊዎች መሆናቸው ን ሲጠቅሱ፣ አንደኛው አቶ ማሙሸት ባቀረቡበት የመስቀለኛ ጥያቄ ከምርጫ በኋላ የወጣቶች ሊግና የኢህአዴግ አባል መሆኑን አምኗል ሲል ጋዜጣው ዘገቧል፡፡ የኢህአዴግ አባል ሆኖም ቢሆን መኢአድን እንደሚደግፍም ገልጾአል፡፡ ዳኛው ‹‹በሁለት ወር ውስጥ እንዴት ብለህ የወጣቶች ሊግ አባል መሆን ቻልክ?›› ብለው ሲጠይቁት ምስክሩ መመለስ ሳይችል ቀርቷል።
የአቶ ማሙሸት አማረ ጠበቃ በበኩላቸው ሶስቱም ምስክሮች አብዛኛዎቹን ጉዳዮች እንደማያስታውሱ በመግለፃቸው የተጠና የምስክርነት ቃል መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ7 አመት በላይ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረው መስቀል አደባባይን ጨምሮ ሰልፉ ተደረገባቸው የተባሉትን ቦታዎች አናውቃቸውም ማለታቸው፣ መተዳደሪያ ስራቸውን መደበቃቸውና መታወቂያ ለማሳየትም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ምስክርነቱ የሀሰት እንደሆነ ስለሚያረጋግጥ ደንበኛቸው በነፃ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment