Monday, August 17, 2015

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት ድርጊቱን ፈጽመናል ወንጀለኞች ግን አይደለንም አሉ


ነኅሴ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ እየሩሳሌም ተስፋው፣ ፍቅረማርያም አስማማውና ደሴ ካህሳይ ልደታ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ፣ የተጠቀሰውን ድርጊት መፈጸማቸውን ነገር ግን ወንጀለኞች አለመሆናቸውን ተናግረዋል። በወጣቶቹ ላይ የቀረበው ክስ ግንቦት 7 የተባለውን አሸባሪ ቡድን ለመቀላቀል ሲሄዱ ማካይድራ በተባለው የድንበር ከተማ ላይ ተይዘዋል የሚል ነው።
ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው አንደኛ ተከሳሽ ብርሃኑ ተክለያሬድ፣ ‹‹ሀገሬ በፋሽስት አምባገነኖች ተይዛ ዜጎች በጨቋኝ ስርዓት ውስጥ ስላሉ ሀገሬንና ህዝቤን ነጻ ለማውጣት ወጣትነቴን ሰውቼ ለመታገል ግንቦት ሰባት ከሚባል ነጻ አውጭ ድርጅት ጋር ለመቀላቀል ወስኜ ወደዚያው አቅንቻለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፣ የግንቦት ሰባት አባል ነኝ፡፡ ወንጀለኛ ግን አይደለሁም›› ሲል ቃሉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ እየሩሳሌም ተስፋው በበኩሏ፣ ‹‹ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፤ ነገር ግን ጥፋተኛ አይደለሁም›› ብላለች፡፡
“ሦስተኛ ተከሳሽ ፍቅረማርያም አስማማው ደግሞ፣ ‹‹ህገ-መንግስቱን አምኜ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ስሳተፍ የደረሰብኝን አውቃለሁ፡፡ ሰላማዊ ትግል እንደማያዋጣም ተረድቻለሁ፡፡ በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚያስፈልገው የነጻነት ትግል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ግንቦት ሰባት ነጻ አውጭን ለመቀላቀል ስጓዝ ማይካድራ ላይ ተይዣለሁ፡፡ ስለዚህ ድርጊቱን ፈጽሜያለሁ፤ ጥፋተኛ ግን አይደለሁም›› በማለት ተናግሯል።
አራተኛ ተከሳሽ ደሴ ካህሳይ በበኩሉ፣ ‹‹አርሶ አደር ነኝ፣ ሰሊጥ አመርታለሁ፡፡ ነገር ግን ያመረትሁትን ሰሊጥ የኢህአዴግ ወታደሮች ይዘርፉኛል፤ መስራት አልቻልኩም፡፡ በዚህ ምክንያት ሌላ ስራ መስራት ስላልቻልኩ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባርን ተቀላቅያለሁ፡፡ ለዚህ ግን ጥፋተኛ አይደለሁም›› ሲል ቃሉን ለፍርድ ቤት ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ቃል ካዳመጠ በኋላ የአቃቤ ህግን አስተያየት የጠየቀ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ ተከሳሾች ጥፋተኝነታቸውን ስላላመኑ ማስረጃ እንዲያቀርብና እንዲያሰማ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ስለሆነም ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ማስረጃን ለመስማት ለነሐሴ 22/2007 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጣው ዘግቧል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment