Thursday, August 13, 2015

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የጦርነት ቀጠና ወደሆነችው የመን መፍለሳቸውን አላቋረጡም

ነኅሴ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያዊያን ሰደተኞች ለሕገወጥ አሸጋጋሪዎች የሚከፍሉት ከ150 እስከ 200 ዶላር ስለሌላቸው፣ ከ600 ኪሎሜትር በላይ ለሁለት ሳምንታት አንዲት የፕላስቲክ ኮዳ ውሃ ብቻ ይዘው በእግራቸው ድንበር አቋርጠው በፑትላንድ ራስገዝ የቦሳሶ የወደብ ዳርቻዎች ይደርሳሉ። የመን ያለው የፀጥታ ሁኔታ አደገኛ በመሆኑ በሌሎች ሕገወጥ አጋቾች እጅ የሚወድቁት ስደተኞች፣ ለአጋቾች የሚከፍሉት ገንዘብ የሌላቸው የአካል ጉዳቶች፣መደፈርና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እንደተፈፀሙባቸው ሂውማን ራይት ወች በሪፖርቱ ጠቁሟል።ይህን ሁሉ ችግር አልፈው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከ600 ኪሎሜትር በላይ ድጋሚ በእግራቸው ተጉዘው ድንበር ጥሰው ይገባሉ። በየመን በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው የመንግስት ጦርና በተቃዋሚዎቹ ሃውቲ አንጃዎች መካከል በሚደረገው ጦርነት ሳቢያ ስደተኞቹ የጥቃት ሰለባ ሆነዋል ብዙዎቹ ሕይወታቸውን አጥተዋል።በሳዑዲ ድንበር አካባቢ ያለው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የቦንብ ጥቃት ደርሶበት ከ45 በላይ ስደተኞች ተገለዋል። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ የየመን ወኪል ቴዲ ተርነር ''በየመን ያለው የፀጥታ ሁኔታ በጣም አደገኛ ነው፣ እንደዚህ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ የትም የለም'' በማለት የስደተኞቹን ስቃይና እንግልት በአጭር ቃል ገልፀውታል። አብዛሃኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ዕድሜያቸው ከ17-30 የሚገኙ ወጣቶች ሲሆኑ በአገራቸው የመኖር ዋስትና ያጡና ለድጋሚ ስደት የተዳረጉም እንዳሉ ሪፖርቱ ገልጿል።የየመን መንግስት አልባ መሆን ለሕገወጥ ስደተኛ አሸጋጋሪዎች ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል ሲል ሶማሊላንድ ፕረስ ዘግቧል።
Source :http://ethsat.com/amharic/%e1%8a%a2%e1%89%b5%e1%8b%ae%e1%8c%b5%e1%8b%ab%e1%8b%8a%e1%8b%ab%e1%8a%95-%e1%88%b5%e1%8b%b0%e1%89%b0%e1%8a%9e%e1%89%bd-%e1%8b%a8%e1%8c%a6%e1%88%ad%e1%8a%90%e1%89%b5-%e1%89%80%e1%8c%a0%e1%8a%93/

No comments:

Post a Comment