Tuesday, July 14, 2015

ሰማያዊ ፓርቲ ከምርጫ በኋላ እየተወሰደ ያለው እስርና ግድያ እንዲቆም ጠየቀ


ሐምሌ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲው ሐምሌ 7 ቀን 2007 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሀገራዊ ‹‹የውሸት ምርጫ›› ከተጠናቀቀበት ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ማግስት በምርጫው በንቃት ይሳተፉ የነበሩና በአስተሳሰባቸው በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ዜጎች በማንአለብኝነት መደብደብ፣ ከሰራ ማፈናቀል፣ ማሰር፣ ማሸማቀቅና መግደል የአገዛዙ ዋና መገለጫ ሆኗል” ብሎአል። ይህንን ድርጊቱን ገዥው ፓርቲ በአስቸኳይ እንዲያቆም ፓርቲው ጠይቋል።
ሰማያዊ ‹‹በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የሰማዊ፣ የመኢአድ፣ የቀድሞው አንድነት፣ የመድረክና የሌሎችም የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በተለዬ ኢላማ ተጠምደው እየተሳደዱ፣ እየተደበደቡና በጅምላ እየታሰሩ አለፍ ሲልም በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ ይገኛሉ›› ሲል ገልጾአል፡፡
አሁን በገዥው አካል እየተወሰደ ያለው ድርጊት ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እናመጣለን የሚለውን አስተሳሰባቸውን የሚያጨልምና የሰላማዊ ትግል አቀንቃኞችን አንገት የሚያስደፋ፣ ይዋል ይደር እንጅ መዘዙም ለማንም ወገን በተለይም ለገዥው መደብ የማይጠቅም መሆኑንም አስታውቋል።
‹‹የአፈናው ስርዓት ብዙ ዓይነት አስተሳሰብና ልዩነት ባለባት ኢትዮጵያ ምርጫን መቶ በመቶ አሸንፌአለሁ ቢልም ሃቁ ግን የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግብዓተ መሬት እየተቃረበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ገዥው ቡድንም የማይክደው መሆኑን በምርጫው ማግስት ጀምሮ የተዘፈቀበት ህዝብን እንደጦር የመፍራት አባዜው ገሃድ አድርጎታል›› ሲል አክሏል።
የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት አሁን ያለው ትግል ‹‹ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ የነጻነት ትግል›› ነው ብለዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም አይ ኤስ ኤስን ለመቃወም መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ “መለስ የሞተው ደንግጦ ነው “ብለው ተናግረዋል የተባሉት ወጣቶች የ3 ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል።
‹‹ኢህአዴግ ሌባ ነው፣ ታፍነናል፣ ታስረናል፣ መለስ የሞተው ደንግጦ ነው፣ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በቁሙ የሞተ ነው፣ ቴዎድሮስ ለህዝብ ነው የሞተው›› በሚል ብጥብጥና ሁከት ፈጥራችኋል፣ የሀሰት ወሬ አውርታችኋል ተብለው የተከሰሱት እነ ሀምሌ 7/2007 ዓ.ም አዲስ ከተማ ምድብ ችሎት አንደኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የ3 ወር እስራት ተፈርዶባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ ‹‹ሰሩት በተባለው ወንጀል በሰውም ሆነ ንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት ባለመኖሩ በዝቅተኛ ወንጀል ይዘነዋል›› ብሏል፡፡ የ3 ወር እስራት ከተፈረደባቸው መካከል አንደኛ ተከሳሽ ቴዎድሮስ አስፋው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ሲሆን፣ ያሬድ ደመቀ እና አንዋር ከድር የፓርቲው አባል አለመሆናቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment