Monday, June 29, 2015

መድረክ ምርጫውን በማስመልከት ቅድመ ሁኔታ አስቀመጠ


ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስባ የሆነው መድረክ ባወጣው መግለጫ በ2007 ዓ ም በሀገራችን ተካሄደ የተባለው ምርጫ በሕግና ሥርዓት ያልተመራና በሕገ-መንግሥቱና በምርጫ ሕጎች የተደነገጉትን የነፃ፣ፍትሐዊና ታአማኒነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መርሖዎች በኃይል በተጣሱበት ሁኔታ የተፈጸመ በመሆኑ መድረክ የምርጫውን ሂደትም ሆነ ውጤት እንደማይቀበለው ገልጾ፣ ለዚህ አሁን ሀገራችን ለገባችበት አስቸጋሪ ሁኔታ መፍትሔ ለማስገኘት የተለያዩ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በጥብቅ እጠይቃለሁ ብሎአል፡፡
በምርጫው ወቅት የታየውን ግዙፍ የሕግ ጥሰት አንድ ወገንተኛ ያልሆነ አካል ተቋቁሞ እንዲያጣራው፣ በ አራት የመድረክ አባሎች ላይ ግድያ በፈጸሙ ወንጀለኞች ላይ ተገቢው ክትትል ተደርጎ ለሕግ እንዲቀርቡና ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው፣ ከምርጫው ቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ በየምርጫ ክልሎቹ የታሰሩት አባሎቻችን ካለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱና የድብደባና የማሰቃየት ተግባራትን የፈጸሙባቸው የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ከምርጫው እንቅስቃሴ ወዲህ ቤታቸው የተቃጠለባቸው፣ የፈረሰባቸውና ንብረታቸው የተዘረፈባቸው አባሎቻቸው ሀብትና ንብረት በአስቸኳይ እንዲመለስላቸውና እንዲከፈላቸው፣ በንብረታቸው ላይ ጉዳት ያደረሱ ካድሬዎችና የጸጥታ ኃይሎች አባላትም በሕግ እንዲጠየቁ፣ በአሁኑ ወቅት በኢህአዴግ ካድሬዎች በማንአለብኝነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈጸሙ የሚገኙት የማሸበር ተግባራት ማለትም በሰላማዊ ታጋዮቻችን ላይ በቀጣይነት እየተፈጸሙ ያሉት ግዲያዎች፣ ማስፈራራት፣ ወከባዎች፣ ዛቻዎችና የመሥራትና የመማር እንዲሁም እርዳታና አገልግሎት የማግኘት መብት በመንፈግ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራት በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንዲደረግና በዚህ አፍራሽና ፀረ ሰላም ተግባራቸው ምክንያት የሀገራችንና የሕዝባችን ሰላምና ደህንነት እንዳይናጋ ወቅታዊ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ መድረክ ጠይቋል።
እንዲሁም ይላል መድረክ በ2007 ዓ ም በሀገራችን የተካሄደው ምርጫ ከሀገራችን ሕገ-መንግሥትና የምርጫ ሕጎች ውጭ መንግሥታዊ ሥልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ሕዝብን በማስፈራራት፣ በኃይልና በአፈና ገለልተኛ ታዛቢዎች በሌሉበት ገዥው ፓርቲ ራሱ ተወዳዳሪ፣ ዳኛና ታዛቢ ሆኖ ያካሄደውና በምንም መልኩ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ያልሆነና ታአማኒነት የሌለው ሕገወጥ ምርጫ
ስለሆነ፣ገዥው ፓርቲ በገለልተኛ የምርጫ አስተዳዳር አማካይነት ገለልተኛ ታዛቢዎች በተገኙበት ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነና ታአማኒነት ያለው ምርጫ ሊካሄድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከመድረክና ሌሎች ሐቀኛ ሰላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በአስቸኳይ በመደራደር ለነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክርሲያዊና ታዓማኒነት ላለው ምርጫ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ፣ በሀገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲረጋገጥ ሕጋዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ፣ እንደዚሁም ነፃ ፍትሐዊ ተዓማኒ ምርጫዎች ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይሳተፉ እንቅፋት የሆኑ ሕጋዊና ተቋማዊ ሁኔታዎችን ለማስወገድ ከኢህአዴግ ጋር ድርድር እንዲካሄድ ጠይቋል።
የሀገራችን ችግሮች እየተወሳሰቡና ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ከሄዱ ኃላፊነቱ የኢህአዴግ ብቻ እንደሚሆን የሚገልጸው መድረክ፣ ኢህአዴግ የፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫን መንገድ ሙሉ በሙሉ በኃይል ቢዘጋም፣ በሕገመንግሥት የተረጋገጡትና ገና ጥቅም ላይ ያልዋሉ የሰላማዊ የትግል ፈርጆችን በመጠቀም አምባገነኑ የኢህአዴግ አገዛዝ ለሕግ የበላይነት እስኪገዛና ሰላማዊ የመፍትሔ ሐሳቦችን ተቀብሎ ሕገመንግሥታዊ መብቶች በተግባር እስኪረጋገጡ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
መድረክ ያቀረበውን የትግል ጥሪ በዝርዝር እቅድ በማውጣት ተግባራዊ ለማድረግ ስለማቀዱ የገለጸው ነገር ለም።

No comments:

Post a Comment