Monday, June 29, 2015

ብአዴን እንደ ሞዴል የሞከራቸው ተቋማቱ በመክሰራቸው ሺዎች ለችግር ተጋለጡ


ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ብአዴን እያስተዳደርኩት ነው በሚለው የአማራ ክልል የጀመራቸው የተለያዩ ተቋማት ውጤት አልባ በመሆናቸው ብዙዎቹ እየፈረሱና ዜጎችን ለችግር እያደረጉ መሆኑን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
የክልሉ ቴክኒክ እና ሙያ ኢንተርፕራይዝ እና የክልሉ ጥቃቅን እና አነሰተኛ ቢሮዎች በክልሉ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ስራ አጦችን በተለያየ ሙያዎች በማሰልጠን የክልሉን የስራ አጥ ቁጥር ከመቀነስ ባሻገር ለልማት አስተዋጽዎ እያደረገ ነው ቢባልም በተግባር እየታየ ያለው የዚህ ተቃራኒ ነው። ተቋሙ በሚልዩኖች ለሚጠጉ ስራ አጥ ወጣቶቸ እና ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል ፈጥሪያለሁ እያለ በየአመቱ ሪፖርት ያቀርባል። ይሁን እንጅ ከ93 በመቶ በላይ የሚሆኑት የተደራጁት የጥቃቅን እና አነስተኛ ወጣቶች ማህበራት ሙሉ በሙሉ መክሰማቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
ከሁሉም ክልሎች የአማራ ክልል ብቻ የጥቃቅንና አነስተኛ ስትራቴጂ መክሸፉን ለፌደራል መስሪያ ቤቱ ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፣ ብዙ የተወራለትን ተቋም ከክስረት ለማዳን የአማራ ክልል ቴክኒክ እና ሙያ ኢንተርፕራይዝ እና የአማራ ክልል ጥቃቅን እና አነሰተኛ ቢሮዎችን በማዋሀድ ካለፉት 4 አመታት ጀምሮ ወጣቶችን ለማሰልጠን ሙከራ ተደርጓል። ይሁን እንጅ ከ4 አመታት ሙከራ በሁዋላ ተቋሙ ሙሉ በሙሉ መፍረሱ ታውቋል። ሁለቱን ተቋማት ለማዋሀድ በተሰራው የማዋቀር ስራ እስከ ገጠር ባሉ ወረዳዎች በነበረው አደረጃጀት 5 ሺ 300 ሰራተኞች ከስራ ውጭ ሆነው ለችግር ተጋልጠው ቆይተዋል።
በሽዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ከተበተኑ እና ይመጣል የተባለው የሚልዮኖች የስራ እድል ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ እንዲሁም የክልሉ ምክር ቤት የበጀተው ከፍተኛ ገንዘብ ውጤት ሳያመጣ በማለቁ የፈረሱት ድርጅቶች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ መወሰኑን መረጃዎች አመልክተዋል።
የክልሉ ንግድና ትራንስፖርት ባለስልጣን ፈርሶ የክልሉ ንግድ ቢሮ እና ትራንስፖርት ባላሰልጣን ቢሮ በሚል አዲስ አደረጃጀት እየተሰራ ሲሆን፣ 4ሺ 397 ሰዎች ከስራ ገበታ ውጭ ሁነዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የማዳበሪያ አቅርቦት ከማህበራት ተቀምቶ ወደ አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም እጅ መግባቱ በማህበራት ህልውና ላይ አደጋ የሚጋርጥ አሰራር መሆኑን የክልሉ አርሶአደሮች ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ልዩ ልዩ ቦታዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች እንደገለጹት ከአሁን በፊት በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት እየመጣ በግማሽ ክፍያና በዱቤ ለማህበሩ አባላት ሲከፋፈል የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት ሙሉ በሙሉ በገዢው መንግስት ስር በሚተዳደረው ንግድ ተቋም መዛወሩ ማህበራትን ፋይዳ በማሳጣት አርሶ አደሩ ግብአቱ በአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በኩል እንዲከፋፈል የተደረገው ‘ ብድር አልከፈላችሁም ‘ በሚል ሰበብ የአርሶ አደሩን ሀብትና ንብረት በመቀማት ባዶ እጅ ለማድረግ እና በቁጥጥር ስር ለማስገባት ሆን ተብሎ በገዢው መንግስት ባለስልጣናት አቀነባባሪነት የተሰራ ደባ እንደሆነ ቅሬታ አቅራቢ አርሶ አደሮች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
የብድርና ቁጠባ ተቋሙ ከአሁን በፊት ለበሬ መግዣ በሚል ለአርሶ አደሩ በከፍተኛ ወለድ ያበደረውን ገንዘብ ለመመለስ መቸገራቸውን የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ አሁንም የማዳበሪያው ሽያጩን በዱቤ ለማቅረብ መሰናዳቱ በአንድ ጊዜ ሁለቱን ብድር ለመክፈል የማይችሉ አርሶ አደሮችን ሀብትና ንብረት በመውረስ ለልመና ብሎም ለስደት ለመዳረግ ሆን ተብሎ የሚሰራ በደል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አስተያየት ሰጭ አርሶ አደሮች ሲናገሩ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ብድሩ እንዲከፈለው የሚጠይቀው ጥር ወር ላይ በመሆኑ ገበሬው ብድሩን ለመክፈል ምርቱን በብዛት ስለሚያወጣ እህሉ ይረክሳል፡፡ይህ መሆኑ ደግሞ ከአሁን በፊት ማህበራት ሲያደርጉት የነበረውን ጊዜ ጠብቆ በተሻለ ዋጋ በመሸጥ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሂደት የሚያሳጣቸው በመሆኑ ብድሩን በቀላሉ ለመመለስ እንደሚያስቸግራቸው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት አርሶ አደሩ እዳውን በመፍራት መሬቱ የሚፈልገውን የማደበሪያ ብዛት ሳይሆን አርሶአደሮች ባላቸው አቅም ብቻ እየዘሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ሁለት ማዳበሪያ የሚፈልገውን መሬት በአንድ ማዳበሪያ ለመሸፈን የሚገደዱት እዳውን በመፍራት መሆኑን የሚናገሩት አርሶአደሮች ፣ ይህም በምርት ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጥር እንደሚችል አክለዋል፡፡ ብድሩን ለመስጠት በሚል ስበብ በየጊዜው ስብሰባ በመጥራት ስራ እያስፈቱት መሆኑን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ ሁሉም አርሶ አደር ሂደቱን ሙሉ በሙሉ የማይቀበለውን ስራ እየሰሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አርሶአደሮቹ የማዳበሪያ አቅርቦቱ ወደ ክልሉ ብድርና ቁጠባ የተዛወረበትን ምክንያት ሲጠይቁ፣ ‹‹ ማህበራት አቅማቸው እንዳይደክም በማሰብና ብድር የማይመልሱ አበላት በመኖራቸው ነው፡፡›› የሚል ምላሽ ከባለስልጣናት እንደተሰጣቸው አስታውሰው፣ የድሃ ድሃ ሆነው አቅም ያጠራቸው ጥቂት አርሶ አደሮች ካልሆኑ በስተቀር ሁሉም ብድሩን በጊዜው እንደመለሰ ይገልጻሉ፡፡
ብአዴን/ኢህአዴግ በአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋሙ አማካኝነት፣ አርሶ አደሩን ከሌሎች የገንዘብ ተቋማት በተለየ እጥፍ ወለድ በማስከፈል በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያከማቸ ሲሆን፣ ገዢው መንግስት አርሶ አደሩን በልዩ ልዩ ግብዓቶች አቅርቦት ሊረዳው ሲገባ የማህበራትን የስራ ድርሻ በመቀማት የፈላጭ ቆራጭነት አሰራሩን በስፋት መጀመሩ ምቾት እንዳልሰጣቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ማናገራቸውን የክልሉ ዘጋቢ ገልጻለች።

No comments:

Post a Comment