Monday, June 29, 2015

የፕሮቪደንት ፈንዱ በገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ለፓርላማ ሳይቀርብ በኮሚቴ እንዲሻሻል ተደረገ


ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግል ሠራተኞች የፕሮቪደንት ፈንድ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ገንዘብ ወደመንግስት በማስገባት ሠራተኞቹ በጡረታ እንዲታቀፉ በሚያስችል መልኩ የተደነገገው የግል ድርጅቶች የማህበራዊ ዋስትና አዋጅ ማሻሻያ በገጠመው ከባድ ተቃውሞ ምክንያት ለፓርላማው ሳይቀርብ በቋሚ ኮምቴዎች ውሳኔ እንዲሻሻል መደረጉን ዘጋቢያችን ገልጿል።
የማሻሻያ ሕጉ ከአንድ ወር በፊት ለፓርላማ ሲቀርብ አሁን በስራ ላይ ያለው ሕግ አንዳንድ ሠራተኞችን የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ ሲያደርግ አንዳንዶቹን ደግሞ በጡረታ ማቀፉ አድሎአዊ አሰራር አስከትሎአል፣ የመብትና የጥቅም ልዩነት ፈጥሮአል በሚል ከሰኔ 16 ቀን 2003 ዓ.ም በፊት ተቀጥረው ይሰሩበት በነበረበት የግል ድርጅት የፕሮቪደንት ፈንድ ያላቸው ሠራተኞች ገንዘባቸው ተወርሶ ወደጡረታ እንዲዛወሩ በረቂቅ አዋጁ መደንገጉ ከተሰማ ወዲህ በርካታ ሠራተኞች የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው መንግስትን አደናግጦአል፡፡
አዋጁ ያጠራቀሙትንና ለአንድ የችግር ወቅት ይሆናል ብለው የሚያስቡትን ገንዘብ ያሳጣናል ብለው የሰጉ ሠራተኞች፣ ከአሰሪዎቻቸው ጋር በመመካከር የፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘባቸውን አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ያወጡ ሲሆን አንዳንድ የሰራተኞቹን ጥያቄ
ያልተቀበሉ አሰሪዎች ባሉባቸው መ/ቤቶች ሠራተኞች በጅምላ ስራቸውን በመልቀቅ የፕሮቪደንት ፈንዳቸውን እየወሰዱ መሆናቸውን መንግሰት በመረዳቱ ጉዳዩ የተመራለት የፓርላማው ቋሚ ኮምቴ አንቀጹ እንዲሻሻልና ሠራተኞች በፍላጎታቸው ብቻ በጡረታ እንዲታቀፉ በረቂቅ አዋጁ እንዲካተት አደርጎአል፡፡
አዋጁ ገና ለሕዝብና የባለሙያዎች አስተያየት እየተሰባሰበበት ሲሆን፣ ለፓርላማው ቀርቦ ሳይጸድቅ ባልተለመደ ሁኔታ አወዛጋቢው አንቀጽ መሻሻሉን በመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንዲነገር መደረጉ ከባድ የሕግ ጥሰት መሆኑን የገለጸው ዘጋቢያችን፣ የመንግሰት እርምጃ በሁኔታው መደናገጡን የሚያሳይ ነው ብሎአል።
የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትናን በሚመለከት የቀረበውንና አሁን የሚሰራበትን አዋጅ ቁጥር 715/2003 ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ም/ቤት ጸድቆ ለፓርላማ የቀረበ መሆኑም አይዘነጋም፡፡
የግል ድርጅቶች ማህበራዊ ዋስትና ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ ሕግ በግል ድርጅቶች ሠራተኞች ሰፊ ተቃውሞ እንዳጋጠመውና ሰራተኞችም ገንዘባቸውን እያወጡ መሆኑን በመጥቀስ መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ
የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሚቀርቡለት አቤቱታዎች ፈጥኖ ውሳኔ መስጠት አለመቻል፣ የመልካም አስተዳደር እና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች አለመቀረፋቸውን ተከትሎ አገልግሎት ፈላጊዎችን በበቂ ሁኔታ ያለማስተናገድ ችግሮች ለገቢ አሰባሰቡ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቅሶአል፡፡ በዚህም ምክንያት የንግዱ ማህበረሰብ በጣም ከሚማረርባቸው ተቋማት መካከል አንዱና ቀዳሚው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የዋና ኦዲተር መ/ቤት በቅርቡ ለፓርላማው ባቀረበው ሪፖርት የአሰራር ዝርክርክነትና ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮች ከሚስተዋሉባቸው መንግስታዊ ተቋማት መካከል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለለስልጣን አንዱ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በገቢ ቀረጥና ታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብን በሚፈቅዱ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት የመንግስትን ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ25 መ/ቤቶችና በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሥር ባሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በድምሩ ከ200 ሚሊየን ብር በላይ በገቢ ግብር፣ ቀረጥና ታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብ በሚፈቅዱ አዋጆች መሰረት ሳይሰበሰብ መቅረቱን አጋልጧል።

No comments:

Post a Comment