Thursday, April 9, 2015

በአዲስአበባ የኤሌክትሪክና ውሃ መቆራረጥ ተባብሶ ቀጥሎአል

  

መጋቢት ፩(ሚያዝያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአዲስአበባ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና የመጠጥ ውሃ መጥፋት ባሳለፍነው ሁለት ሳምንታት ተባብሶ መቀጠሉ ህብረተሰቡን ለተለያዩ ወጪዎችና እንግልት እየዳረገ መሆኑንና በዚህ ጉዳይ መንግስት የሚሰጠውን መግለጫ ማመን የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በተለይ ባለፈው ሳምንት እና በያዝነው ሳምንት የኤሌክትሪክ ኃይል ለረጀም ሰዓታት እንደሚጠፋ ተናግረዋል፡፡ በአዲስአበባ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጡ በአንድ ጊዜ ድፍን ከተማዋን የሚሸፍን መሆኑና የሚቆበት ጊዜም ወደአንድ ሙሉ ቀን ወይንም ሌሊት መቀየሩ ደግሞ ግራ የሚያጋባ መሆኑ ታውቆአል፡፡
የመጠጥ ውሃ መቆራረጥም ከጊዜ ወደጊዜ ሊሻሻል ይችላል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸው፣  ነገርግን በአሁኑ ሰኣት ውሃ የማይኖርባቸው ቀናት እየጨመሩ መምጣታቸው አሳሳቢ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ አንድ በካዛንቺስ አካባቢ በአነስተኛ ምግብ ቤት ንግድ የሚተዳደሩ ነዋሪ ውሃ የሚጠፋባቸው ቀናት በአሁኑ ወቅት በተከታታይ ለሶስትና ለአራት ቀናት እየሆነ መምጣቱ አስደንግጦናል ካሉ በኃላ፣  ኤሌክትሪክም ቢሆን ደጋግሞ መቆራረጡ ምግብ ለማብሰል ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ወጪና ኪሳራ እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  አያይዘውም ውሃ መጣ ሲባል ኤሌክትሪክ እየጠፋ፣ ችግሩም ዕለት ከዕለት እየተባባሰ ኑሮአችንን እያመሰቃቀለ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ ከኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ በርካታ አገልግሎት ሰጪ መንግስታዊ መ/ቤቶች ስራ እየተደናቀፈ ከመሆኑም በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች የኤክስፖርት ትዕዛዝ ማሟላት አለመቻልና ሠራተኞቻቸውን እስከመቀነስ አድርሶአቸዋል፡፡ “በመንግስት በኩል ችግሩን እየፈታን ነው፣ አዳዲስ የውሃ ጉድጓዶች እየቆፈርን ነው፣ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችን በአዲስ እየቀየርን ነው” ከማለትና ተስፋ ከመስጠት ያለፈ ችግር ፈቺ መፍትሔ እየሰማን አይደለንም ያሉት ነዋሪዎቹ፣ አሁን አሁን ችግሩን ለመፍታት መንግስት አቅም እንደሌለው እየተረዳን በመምጣታችን ከንግግሮቻቸው ምንም ቁምነገር መጠበቅ ትተናል ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ መሰረታዊ የህዝብ ችግሮች ይበልጥ የመጪው ምርጫ ጉዳይ እያሳሰበው በመሆኑ፣ ከምርጫው በፊት መፍትሔ የማግኘታቸው ነገር እንዳሳሰባቸውም ያነጋገርናቸው ወገኖች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ከከተማው ሕዝብ ከ75 በመቶ በላይ 24 ሰኣታት ውሃ ያገኛል ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡
Source: ethsat.com

No comments:

Post a Comment