Wednesday, April 27, 2016

ዜጎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መፍለሳቸውን ቀጥለዋል


ሚያዚያ ፲፱(አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙና በምእራባውያን የአኗኗር ዘዴ የሚኖሩ ጥቂት ግለሰቦች የመኖራቸውን ያክል፣ ተገኘ የሚባለው የኢኮኖሚ እድገት የዘለላቸው ወይም ፈጽሞ ያላያቸው እጅግ በርካታ ዜጎች ስደትን እንደአማራጭ በመውሰድ ባህር እና በረሃ አቋርጠው ወደ አረብ አገራት ወይም ወደ አውሮፓና አሜሪካ ሲሰደዱ ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። ጉልበቱ የሌላቸው አቅመ ደካሞች ደግሞ ወደ ዋና ዋና የክልል ከተሞች ተሰደው በልመና ህይወታቸውን በመግፋት ላይ ናቸው። ብዙውን ጊዜ የከተሞችን ገጽታ ያበላሻሉ፣ የልማታዊ መንግስቱን ስም ያጎድፋሉ በሚል ከከተሞች እየታፈሱ ወደ ተለያዩ ቦታዎች እየተወሰዱ ይጣላሉ። በተለይ ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ ዜጎች በርሃብ መጠቃታቸውን ተከትሎ፣ የቻሉት ወደ ከተሞች ተሰደው ችግሩን ለማሳለፍ ቢሞክሩም ፣ በመንግስት ካድሬዎች ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል። ቀያቸውን ለቀው እንዳይሄዱም፣ በጸጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
በአዲስ አበባ ውስጥ በተናጠል የሚመጡና በልመና ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ሁሉንም የእድሜ ክልልና ጾታዎች የሚያካትት ነው። የኢሳት ካነጋገራቸው ዜጎች ለመረዳት እንደሚቻለው ብዙዎቹ ተሰደው የመጡት ከአማራ ክልል ነው።
በሰሜን ሸዋ ዞን በደራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑና በአዲስ አበባ በልመና ህይወታቸውን ለማቆየት የሚጥሩት እናት እንደተናገሩት፣ በአካባቢያቸው የገባው ረሃብ ከፍተኛ በመሆኑ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። መንግስት በቂ እርዳታ ለመስጠት ባለመቻሉ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት መገደዳቸውን ገልጸዋል
ከአዊ ዞን እንደመጡ የተናገሩት ሌላ እናት በበኩላቸው፣ ችግሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ፣ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ለመለመን መገደዳቸውን ተናግረዋል።
የማዳበሪያ እዳ አስመርሯቸው መምጣታቸውን የሚናገሩት አንድ አዛውንት፣ ለምነው በሚያገኙት ገንዘብ እዳቸውን ለመክፈል ማሰባቸውን ይገልጻሉ
የሚጦሩዋቸው ልጆች በማጣታቸው ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ የሚናገሩ ሌላ አዛውንት፣ በአዲስ አበባ ህዝቡ ምጽዋት እየሰጠ እያኖራቸው መሆኑን ተናግረዋል

No comments:

Post a Comment