Monday, April 11, 2016

የሶስት ኢትዮጵያውያን ንብረት ነው የተባለ 356 ሺ ዶላር በቻይና የጉአንግዙ መገኘቱን የቻይና መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ


ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2008)
በቻይና የጉአንግዙ ግዛት በሚገኝ አንድ አለም-አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የሶስት ኢትዮጵያውያን ንብረት ነው የተባለ 356 ሺ ጥሬ ዶላር መገኘቱን የቻይና መገናኛ ብዙሃን ሰኞ ዘገቡ።
በአንድ ሻንጣ ተሞልቶ የነበረው ይኸው ከፍተኛ ገንዘብ በአየር መንገዱ መሳፈሪያ አካባቢ ለጉዞ በነበሩ ሁለት የኮንስትራክሽን ሰራተኞች መገኘቱንና የንብረቱ ባለቤት ናቸው ለተባሉት ሶስቱ ኢትዮጵያውያን መሰጠቱ ታውቋል።
356ሺ ጥሬ ዶላር ገንዘብን የያዘው አነስተኛ ሻንጣ በዋናው የአየር ማረፊያው መግቢያ ላይ መገኘቱንና ሁለቱ ግለሰቦች ለፖሊስ ማስረከባቸውን የቻይናው ዜና አገልግሎት ዢንሁዋ ሰኞ ዘግቧል።
የሻንጣው ባለቤት አድራሻ ለማግኘት በማሰብ ሁለቱ ቻይናውያን ሻንጣውን ቢፈቱም አይተውት የማያውቁት ገንዘብን በሻንጣው በማየታቸው ድንጋጤ እንዳደረባቸውና ገንዘቡን ለፖሊስ እንዳስረከቡ ቻይናውያኑ አስረድተዋል።
ገንዘቡን የቆጠሩት የቻይና የጸጥታ ሃይሎችም የገንዘቡ ባለቤት ናቸው ለተባሉ ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ያስረከቡ ሲሆን፣ የሶስቱ ኢትዮጵያውያን ማንነት ግን ይፋ አልተደረገም።
ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ በበርካታ ሃገራት በጥሬ ይዞ መንቀሳቀስ የማይፈቀድ ቢሆንም፣ የቻይና የጸጥታ ሃይሎች ግን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የሰጡት ዝርዝር የለም።
የባለ መቶ ኖቶቹን 356ሺህ ሶላር (ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ) የያዙት ኢትዮጵያውያን ገንዘቡን ለምን ጉዳይ እንደያዙትና ለምን አላማ ሊያዉሉት እንደነበርም የቻይና ፖሊሶች የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሶስት ቀን ወደ ቻይናው ጓንጉዙ አየር ማረፊያ በረራን እንደሚያደርግ ለመረዳት ተችሏል።
ከወራት በፊት በአውሮፕላን እቃ መጫኛ ክፍል ውስጥ ተደብቆ ስዊድን ሃገር ከገባ በኋላ በሃገሪቱ የፖለቲካ ጥገኝነትን የጠየቀ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ በመንግስት ባለስልጣናት ዶላር በሻንጣ እየተደረገ እንደሚወጣ ለኢሳት መግለጹ ይታወሳል።
ከኢትዮጵያ ጋር የቅርብ ወዳጅነት አላት በምትባለው ቻይና በርካታ በለስልጣናት ለተለያዩ ጉዳዮች በየጊዜው እንደሚጓዙባትም ይነገራል።

No comments:

Post a Comment