Monday, April 11, 2016

በአፋርና በኢሳ ጎሳዎች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ



በአፋር ክልል ገዋኔ ወረዳ በአፋርና በኢሳ ሶማሊ ጎሳዎች መካከ ግጭት ተቀስቅሶ በግንሹ የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉንና በርካታ ሰዎችም ለጉዳት መዳረጋቸውን የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ሰኞ ገለጠ።
በወረዳው አስጊታ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተቀሰቀሰው ይኸው ግጭት አንድ የአፋር ተወላጅ ወጣት በኢሳ ሶማሊ ጎሳ መገደሉ ተከትሎ እንደሆነ የድርጅቱ ሃላፊ የሆኑት አቶ ገሃስ መሃመድ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
በአካባቢው ሰኞ ምሽት ድረስ የተኩስ ልውውጥ በመካሄድ ላይ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሎ ስጋት መኖሩን ሃላፊው አስታውቋል።
በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ለዘመናት ሲቀርቡ የነበሩ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች እልባት ባለማግኘታቸው ምክንያት በወረዳው ውጥረት ሰፍኖ እንደሚገኝም የሰብዓዊ መብት ድርጅቱ ሃላፊ የሆኑት አቶ ሃጎስ መሃመድ ተናግረዋል።
ሁለቱ ጎሳዎች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከግጦሽ መሬት ጋር በተገናኘ በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ይገቡ እንደነበር ያወሱት ሃላፊው በአካባቢው መነሳት የጀመሩ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግስት ሃላፊዎች በኩል ችላ መባላቸው ሳቢያ ግጭቱ በአዲስ መልክ መቀጠሉን አስረድተዋል።
በዚሁ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ውጥረት አፋጣኝ እልባትን ካላገኘም ተመሳሳይ ግጭቶች መከሰታቸው እንደማይቀር የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት አክሎ አመልክቷል።

No comments:

Post a Comment