Sunday, January 17, 2016

በሰርጉ ዋዜማ በጥይት የተመታው መምህር ፍጹም አባተ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና ተደረገለት


ኢሳት (ታህሳስ 5 2008)

በኢሊባቡር መቱ በሰርጉ ዋዜማ በጥይት የተመታው መምህር ፍጹም አባተ ህይወቱ አስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከቤተሰቦቹ የተገኘው መረጃ አመለከተ።

ታህሳስ 29 ቀን 2008 ዓ ም ጭንቅላቱን በጥይት የተመታው መምህር ፍጹም፣ በመቱ ሆስፒታል ከታየ በኋላ ለከፍተኛ ቀዶ ጥገና ሕክምና ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከዚያም ወደ ወደአለርት ሆስፒታል ተልኮ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ወደ ጥቁር አንበሳ ተመልሶ ቀዶ ጥገና እንደተደረገለት ለማወቅ ተችሏል።

በጥቁር አንበሳ በዛሬው እለት ቀዶ ጥገና የተደረገለት ፍጹም አባተ፣ የማየት እድሉ ከ 5-10 ፐርሰንት እንደሆነ ቀዶ ጥገናውን ያደረጉ ሃኪሞች መናገራቸው ታውቋል።

ጭቅላቱን በጆሮ በኩል በኋላ የተመታው መምህር ፍጹም፣ ቀዶ ጥገና ከተደረገለት በኋላም ቢሆን ብዙ መናገር እንደማይችል ቤተሰቦቹ ለኢሳት አስረድተዋል።

በሙሽራው ላይ የተኮሱት የመንግስት ወታደሮችም በህግ ቁጥጥር ስር ላይ ናቸው እንደተባሉ የሙሽራው አባት አቶ አባተ ለኢሳት ገልጸዋል። ወታደሮችም ለምን ይህንን አይነት የጭካኔ እርምጃ እንደወሰዱ የሚታወቅ ነገር የለም ተብሏል።

የቤተሰቡ ሶስተኛ ልጅ የሆነውና ለ8 ዓመት በመምህርነት ያገለገለው ፍጹም አባተ፣ አጥንቱ ከመሰበሩም በተጨማሪ፣ ደም ወደውስጥ እንደፈሰሰበትም ወላጅ አባቱ አቶ አባተ ለኢሳት ገልጸዋል።

“በልጄ ላይ ደረሰው አደጋ በማንም ላይ እንዳይደርስ እፈልጋለሁ” ያሉት የመምህር ፍጹም አባት አቶ አባተ፣ የህክምናውን ወጪ የሚሸፍኑት በእድሜ የገፉ የፍጹም አባትና ቤተሰቦቻቸው እንደሆኑ ለኢሳት ተናግረዋል።

የመምህር ፍጹም እጮኛ ወ/ሪት ፍሬህወት በበኩሏ አደጋው እጅግ በጣም አስደንጋጭ ሁኔታ እንደፈጠረባት ለኢሳት ገልጻለች።

ሰለአደጋው በስልክ ከሙሽራው እህት እንደተደወላት የተናገረችው ወ/ሪት ፍሬህወይት፣ መኪና ተፈልጎ ከበቹ ወደ ቡሪሳ ሌሊት እንደመጣችና ተጎጂ እጮኛዋን ማየት እንደቻለች አስረድታለች።

ወ/ሪት ፍሬህይወት በለጠ የኢትዮጵያ ህዝብም ጸሎት እንዲያደርግ ጠይቃለች።

መምህር ፍጹም፣ በስራው እጅግ የተከበረና በተማሪዎች ዘንድም በጣም ተወዳጅ እንደሆነ የተለያዩ ሰዎች መስክረዋል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment