Wednesday, November 4, 2015

ብአዴን የተነሳበትን አቅጣጫ መሳቱ ተነገረ፡፡

ጥቅምት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ብአዴን በአሁኑ ጊዜ የደረሰበት ደረጃ ሁሉንም ነገር በዘመድ አዝማድ የሚሰራበት የተሳሳተ አቅጣጫ የተከተለበት ሁኔታ ላይ መድረሱን ነባር ታጋዮች ተናገሩ፡፡
ከመጀመሪያዎቹ የትግል ዓመታት ጀምረው እስከ ድሉ ማግስት ድረስ ለድርጅታቸው ታማኝ በመሆን የአካልና የህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ የቀድሞ ታጋዮች እንደተናገሩት ፤በስርዓቱ ከጥቃቅን ነገሮች ጀምሮ እሰከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ ጉዳዮች ካለሙስና የማይሰራበት ደረጃ መድረሱ እንዳሳዘናቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
‹‹ በክራይ ሰብሳቢነት መስክ የተሰማሩ አመራሮች አሉ፡፡ ›› የሚሉት ታጋዮች የቀድሞ አባላትን በማራቅ በአሁኑ ሰዓት በስልጣን ላይ የሚገኙት አመራሮች የራሳቸውን ጥቅም ከትንሽ እስከ ትልቅ በማሳደድ ስራ በመጠመዳቸው ሌላውን ባለበት እንደተውት ተናግረዋል፡፡ አሁንም ሞራላቸውን የሚነካ አመራር መኖሩ እንዳሳዘናቸው የሚናገሩት ታጋዮች በነገሮች ተስፋ በመቁረጥ ሁሉንም በዝምታ ለማለፍ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡-
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ የቀድሞ ታጋይ ሲናገሩ ‹‹ ደርግን የታገልነው ሁሉም በነጻነት፣በእኩልነትና በፍትሃዊነት ለማኖር የሚቻልባት ሃገር ለመፍጠር ቢሆንም በሐገሪቱ የተንሰራፋው ክራይ ሰብሳቢነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የስርዓቱ አቅጣጫ ከመዛባቱ የመነጨ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ያሉ አመራሮች ታጋይንም ሆነ ትግልን የማይወዱ የማይደግፉ በመሆናቸው ሁሉም በሙስናና በክራይ ሰብሳቢነት መስመር ተሰማርተው መታየታቸውን የሚገልጹት ታጋይ ፣ ከጽዳት ጀምሮ የስራ ቅጥር የሚከናወነው በወገንና በሙስና በመሆኑ አሳዛኝ ደረጃ መድረሱን ገልጸዋል፡፡ብአዴን ኢህአዴግ የተነሳበትንና የታገልንለት ዓላማ መስመሩን ስቷል የሚሉት ቀደምት ታጋዮች ትግሉ አቅጣጫውን በመሳቱ የታሰበው ሁሉ በመፍረስ ላይ እንዳለ በግልጽ የሚያሳይ ምልክት እየታየ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
‹‹ በየጫካው የወደቅንለት ትግል ዛሬ በክራይ ሰብሳቢዎች ተጥለቅልቆ ተበርዟል ፡፡ ›› የሚሉት ሌላዋ ታጋይ፣ አሁን አመራሮ ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ በእከከኝ ልከክህ መርህ በመተብተብ ትግሉን እየጣሉት እንደሆነ በሃዘን ገልጸዋል፡፡በክራይ ሰብሳቢነት መስመር የሚገኙ የበታች አመራሮችን የተቆራረጠ እርምጃ በመውሰድ ከመታገል ይልቅ የነበራቸውን ግንኙነት በመመልከት ከአንድ ከተማ አንስቶ ወደ ሌላ ከተማ በነበረው የስራ ደረጃ ማዛወር ለሰሩት ስራ ድጋፍ የመስጠት ሁኔታ መታየቱ ህዝቡን ከድርጅቱ እየለያየው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ሊወድቅ የሚችልበት ሁኔታ መጋረጡን የሚናገሩት ነባር ታጋዮች፣ አቀንቅኖ ያለውና ሃገሪቱን እየጎዳት ያለው ክራይ ሰብሳቢነት አደጋ ህዝቡን ከድርጅቱ እየነጠለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ክራይ ሰብሳቢነትና ሙሰኝነት እየጠነከረ በሄደ ቁጥር መንግስትና ህዝብ እየተለያዩ እንደሚሄዱም አክለው ተናግረዋል፡፡ ከላይ አመራሩ ጀምሮ በትንሽ ነገር የመርካት ሁኔታ ይታይባቸዋል የሚሉት ሌላዋ የቀድሞ ታጋይ የተጀመሩ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም በክራይ ሰብሳቢነት መስመር ያለውን ሂደት ድርጅቱ ሊቋቋመው አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
“ልማትና እድገት ማለት ህንጻ መስራት ቢሮ መገንባት አይደለም፤የጤና ጣቢያ ህንጻዎችም ይሰራሉ፡፡ሁኖም በአመራሩ ላይ ሊሰራ የሚገባው የአመለካከት ለውጥ አለመምጣቱ ትልቅ ችግርነው” የሚሉት የቀድሞ ታጋይ ፣ ‹‹ ይሄን ሰርቻለሁ ፣ይሄ ይቀረኛል የሚለው ንግግር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ተለውጦና ለውጦ ማሳየት ከከፍተኛ አመራሩ ይጠበቃል ›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ከቀበሌ ጀምሮ እሰከ ላይ ድረስ በአሁኑ ሰዓት ያሉ አመራሮች ህብረተሰቡን በማስተናገድ ፋንታ በስብሰባ ተጠምዶ የመዋል ሱስ ከተጠናዎታቸው ሰንብተዋል ›› የሚሉት ታጋይ፣ በስብሰባ ብቻ የሃገር ችግር እንደሚፈታ ማሰባቸው አሳዛኝ መሆኑን አክለዋል፡፡
ብአዴን በቀጣዩ ወር ላይ ለሚያከብረው በዓል ድምቀት የሆኑልኛል ያላቸው የቀድሞ ታጋዮች በድርጅታቸው እያፈሩ መሆኑን በተደጋጋሚ በመናገር ድርጅቱ ያሰበውን የቅስቀሳ ስራ እንዳይሳካለት ማድረጋቸው ማንነቱን ገሃድ ያወጣ ሃሳብ መሆኑን ታዛቢዎች በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡
ብአዴን በከፍተኝ ድርቅ በተጠቃው የአማራ ክልል ለሚያከብረው በአሉ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደርጋል። አብዛኛውን የበአል ወጪ በግድ ከህብረተሰቡ በሚሰበሰብ ገንዘብ ለመሸፈን ማቀዱን ምንጮች ገልጸዋል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment