Thursday, November 5, 2015

የፌዴሬሽኑ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የገዢው ፓርቲ አባል ናቸው” አትሌት ከላሊ ንጉሴ አብርሃ

ከላይ ንጉሴ ይባላል፡፡ የረዥም ርቀት እና ማራቶን ሯጭ ሲሆን አሁን የሚገኘው በስደት ቶሮንቶ፣ ካናዳ ውስጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በነበረበት ወቅት ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ያሳለፈውን የህይወት ተሞክሮ በማስመልከት ከኢትዮጵ ዛሬ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
ኢ.ዛ.፡- በቅድሚያ ይህን ቃለመጠይቅ እንድናደርግ ፈቃደኛ በመሆንክ በትዝታ ጋዜጣ ስም እያመሰገንኩ፤ እሰቲ እራስክን በማስተዋወቅ እንጀምር፡፡ የት እንደተወለድክ ፣ ሙያህን እና የአስተዳደር ሁኔታክን ግለፅልኝ
አትሌት ከላሊ፡- ከላይ ንጉሴ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት ራያ ከሚባል አካባቢ ሲሆን ትንሽዬ ገጠር ውስጥ ነው፡፡ እድገቴም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሲሆን እዛው ራያ አካባቢ ነው፡፡ ትምህርቴንም ቢሆን እስከ ሁለተኛ ደረጃ እዛው ነው የጨረስኩት፤ በሙያ ደግሞ የረዥም ርቀት እና የማራቶን ሯጭ ነኝ፡፡
ኢ.ዛ.፡- ትንሽ ስለ ራያ ህዝብ እና አካባቢው ብትነግረኝ?
አትሌት ከላሊ፡- ራያ የሚገኘው በትግራይ ክልል ሲሆን፤ በህዝብ ቁጥር እንዲሁም በመሬት ይዞታው በክልሉ ደረጃ ሰፊ ነው ሊባል ይችላል፡፡ የራያ ህዝብ ዋነኛ መተዳደያው በእርሻ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰፋ ያለ ይዞታ ቢኖረውም ህዝቡ ግን ከፍተኛ የሚባል በደል የደረሰበት ነው፡፡ ራያ በትግራይ ክልል የተካለለ ቢሆንም የተገለለ አካባቢ ይመስላል፡፡ እንደሌሎቹ የትግራይ ግዛቶች የልማት እንቅስቃሴ ተጠቃሚ ሊሆን አልቻለም፡፡
ኢ.ዛ.፡- አካባቢው የልማት ተጠቃሚ አይደለም ስትል ምሳሌ ልትጠቅስልኝ ትችላለክ?
አትሌት ከላሊ፡- ለምሳሌ በከተማ እድገት ብንመለከት ማይጨው የራያ ዋና ከተማ ነው፡፡ እንደዋና ከተማነቱ ይኼ ነው የሚባል መሻሻል ወይም እድገት እንዲሁም ለእድገቱ የሚያስፈልጉ ከመንግስት የሚደረጉ አቅርቦቶች የሉም፡፡ ሌሎች በትግራይ ክልል የሚገኙ አካባቢዎችን ብንመለከት ልዩነቱን መገንዘብ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ ያክል አዲግራት ወይም ኡቅሮ የሚባሉ አካባቢዎች በአማካይ አንድ አይነት የህዝብ ቁጥር እና የመሬት ስፋት ይዘው ግን በመሀከላቸው ያለው የመሰረተ ልማት እንቅስቃሴ እጅግ በጣም ሰፊ ነው፡፡ አንድ መሰረተ ልማት ብናነሳ እንኳን፣ ህክምናን ብንመለከት በራያ አካባቢ ማይጨው የሚባል ቦታ ላይ አንድ መካከለኛ የሚባል ሆስፒታል ነው የሚገኘው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ ይኸው አሁን ከ20 አመት በላይ አሳልፏል፤ ራያን በሚያክል አካባቢ አንድ ክሊኒክ ብቻ፣ አስበው ከተለያዩ የራያ ክፍሎች ሰው ታሞ የሚመጣው እዚችው ሀኪም ቤት፣ እዛ ድረስ እስኪደርስ ያለውን እርቀት፣ መንገድ ላይ የሚሞትም አለ፣ እንደዛም ሆኖ ብትደርስ ብዙ ጊዜ ወደሌላ የትግራይ አካባቢዎች ለሚገኝ ሆስፒታል ሪፈር ትደረጋለክ፡፡ የሌሎች አካባቢ እንቅስቃሴዎችን የማየት እድሉን ስላገኘው ከራያ ጋር ሳመዛዝነው ውስጤ ያዝናል፡፡ ይኼም ሳያንስ መንግስት እንዲህ እና እንዲያ እያደረኩ ነው ብሎ በሚዲያ ሲናገር ጉዳዩን ለምናውቀው የሚያሳዝን ነው፡፡
ኢ.ዛ.፡- በቋንቋ ስንመለከት ራያ በሦስት የተከፈለ ነው ብለው የሚናገሩ አሉ ይኸውም የአማርኛ ተናጋሪ፣ የኦሮምኛ እንዲሁም የትግርኛ ተናጋሪ፤ ሦስቱም አንድ ላይ ተጠቃለው ነው ወይስ እንደቋንቋቸው አካባቢያቸውም ይለያያል?
አትሌት ከላሊ፡- ራያን በአጠቃላይ ስንመለከተው በሁለት ልንከፍለው እንችላለን፤ ይኸውም ራያ ቆቦ የሚባለው ወደ አማራ አካባቢ የሚገኘው ሲሆን በአብዛኛው የአማርኛ ተናጋሪ ያለበት ክፍል ሲሆን፤ እኔ ወደምኖርበት አካባቢ ያለው ደግሞ ራያ አዘቦ የሚባለው አካባቢ ሲሆን ትግርኛ፣ አማርኛ እንዲሁም ኦሮምኛም ተናጋሪዎች ያሉበት ነው፡፡ እንዲህ ቢከፋፈሉም ያው እንደ አንድ ክልል ነው የሚታወቁት፡፡
ኢ.ዛ.፡- ወደ አትሌቲክሱ ህይወትክ እንመለስ እና እንዴት ወደ ሩጫው ገባህ?
አትሌት ከላሊ፡- ፕሮፌሽናል የአትሌቲክስ ህይወት የጀመርኩት እዛው ራያ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡ በጊዜው የከፍተኛ ሁለተኛ ተማሪ ነበርኩኝ ጊዜውም ወደ 1999 ዓ.ም. አካባቢ መሆኑ ነው፡፡ በጊዜው ከተለያዩ ወረዳዎች የተወጣጡ ሯጮች በክልሉ በተካሄደው ውድድር ይሳተፉ ነበር፡፡ እኔም የምኖርበትን ወረዳ በመወከል ለመሳተፍ በቃሁ፡፡በጊዜው ጥሩ የሚባል ሰዓት በማስመዝገቤ ከዛን ጊዜ በኋላ በሌሎች ውድድሮችም እንድሳተፍ ተደረኩኝ ማለት ነው፡፡
ኢ.ዛ.፡- እንደሚታወቀው እትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በብዙ የሚቆጠሩ ወጣት አትሌቶችን ታፈራለች፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ ችሎታ ኖሯቸው እንኳን እድሉን አግኝተው ወደ ከፍተኛ መድረኮች ወጥቶ ለመወዳደር በራሱ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንባቸው በየጊዘው የሚሰማ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ አንተም ከእነሱ አንዱ እንደመሆንክ እንዴት እድሉን አገኝተክ ልትወጣ ቻልክ?
አትሌት ከላሊ፡- እርግጥ ነው ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት፤ የኔም ጉዳይ ቢሆን እድል ተጨምሮበት እንጂ ሚናልባትም እዛው እቀር ነበር፡፡ ወረዳ ላይ ከተሳተፍኩ በኋላ ሌሎች ውድድሮችም ላይ አመርቂ ውጤት በማስመዝገቤ የትግራይ ክልልን ወክዬ እንድሳተፍ ተደረኩኝ፡፡ ከዛም ወደ አዲስ አዲስ አበባ በመምጣት ትግራይን ወክዬ ተወዳድሬያለሁ፡፡ በይበልጥ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2002/2003 ዓ.ም. ጥሩ ፐርፎርማንስ አሳይቼ ነበር በዚህም የተነሳ ማረሚያ ለሚባል የስፖርት ክለብ ውስጥ ለመሮጥ በቃሁ፡፡ እዛ በነበርኩበትም ወቅት በተለያዩ ውድድሮች ላይ የተሳተፍኩ ሲሆን ይኸውም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ በበርካታ መድረኮች ላይ ለመወዳደር ችያለሁ፡፡
ኢ.ዛ.፡- በተለያዩ ሀገራት የመወዳደር እድል እንዳገኘክ ነግረኸኛል፤ እንዴት ነበር በግልክ ነው ወይስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመቻችቶልክ ነው?
አትሌት ከላሊ፡- በእርግጥ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው በውድድሩ ላይ እንድንሳተፍ የሚያደርገው፡፡ ይሁን እንጂ የምትወዳደርለትን ክለብ ወይም ሀገርህን አልያም ደግሞ በግልቅ መሳተፍ ትችላለክ፡፡ ዋናው ነገር በቅርብ ጊዜያት የምታስመዘግበው ውጤት ይወስነዋል፡፡ ለምሳሌ በረዢም ርቀቶች ላይ ስትሳተፍ ቢያንስ ጥሩ ሰዓት እና ከ1-7 ወይም እስከ 8ኛ ደረጃ ላይ የሚወጡት ሯጮች ቅድሚያ ያገኛሉ፡፡ ሀገር እንዲወክሉ ይደረጋል ማለት ነው፡፡
ኢ.ዛ.፡- ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በተያያዘ በርካታ መረጃዎችን እንሰማለን፤ ይኸውም እኩል የሆነ እድል ለሯጮች አይሰጥም፣ በሙስና የተጨማለቀ ነው፣ በብሔር የተከፋፈለ ነው፣ ሯጮች በሀገር ውስጥ እድል ሳይሰጣቸው ለሌላ ሀግር እየሮጡ ውጤት እያመጡ ነው እና የመሳሰሉ ቅሬታዎችን፤ ከዚህ አንፃር አንተስ የታዘብከው ወይም የደረሰብክ ነገር አለ?
አትሌት ከላሊ፡- በቅድሚያ የሰማኸው መረጃ ትክክል መሆኑን እኔው እራሴ ላረጋግጥልክ እወዳለው፡፡ ያው በየጊዜው የምንመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ እንደው በቅርቡ እዛ በነበርኩበት ጊዜ የተከሰተውን አንድ ጉዳይ ብነግርክ፤ የሴቶች የረጅም ሩጫ ተካሂዶ ነበር፡፡ ታዲያ ውጤት ያመጡትን ይመርጣሉ ብለን እየጠበቅን 2ኛ ነው 3ኛ የወጣችውን ጥለው ውድድሩ ላይ አቋርጣ የወጣችውን ተወዳዳሪ መርጠዋል፡፡ እሷም ሄዳ ውጤት አላመጣችም በውድድሩ 24ኛ ነበር የወጣችው፡፡ ይህ እንግዲህ እኔ በቅርቡ የታዘብኩትን ነው የነገርኩህ፡፡ ይህ የሚያሳየው ፌዴሬሽኑ ምን ያክል በዝምድና፣ በሙስና፣ በብሔር እና በፖለቲካ አቋምህ እንደሚወሰን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አትሌቲክሱ አያድግም፣ ለታዳጊዎች እድል አይሰጡም ከዚህ የተነሳ ይኸው የድሮ ዝናውን እያጣ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ብዙ ችግር አለበት፤ እውነተኛ ነገር እየተሰራ አይደለም፡፡ የመወዳደር አቅም እና ችሎታ እያለክ፣ ውድድር አግኝተክ፣ ኢንቪቴሽን ወረቀት መጥቶልክ እንኳን በውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ብር ጉቦ መስጠት አለብክ፡፡ ይህን ደግሞ ማድረግ የሚችሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡
ኢ.ዛ.፡- እንደገለፅክልኝ ይህ የሚያሳየው በፌዴሬሽኑ ውስጥ ከፍተኛ የሚባል ችግር እንዳለ ነው፡፡ ታዲያ አትሌቶቹስ ይኼን እያዩ እንደው ዝም ብለው ያልፋሉ፤ ተሰባስበው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አለ ከዚህ አንፃር?
አትሌት ከላሊ፡- የአትሌቶች ማህበር የተቋቋመ አለ፡፡ ሁሉንም አትሌቶች ያቀፈ ማለት ነው፡፡ ሰብሳቢዎቹም ትላልቅ የሚባሉ አትሌቶች ናቸው፡፡ በየጊዜው ስብሰባ ይደረጋል፣ ችግሮች ይነሳሉ፣ መፍትሄ ተብሎ ይወራል ነገር ግን እስካሁን ምንም ሊፈጥሩ አልቻሉም፡፡ አሁንም ችግሮቹ እንዳሉ ናቸው፡፡
ኢ.ዛ.፡- ፌዴሬሽኑ ከገዢው ፓርቲ ጋር በተያያዘ ባለው የፖለቲካ ትስስር ሲታማ ይሰማል፡፡ ለምሳሌ የቴክኒካል ዳይሬክተሩ አቶ ዱቤ ጁሎ የኢህአዴግ አባል መሆናቸው በራሱ ትልቅ ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንተ ምን አስተያየት አለህ?
አትሌት ከላሊ፡- እውነቱን ለመናገር ዳይሬክተሩ ብቻ ሳይሆኑ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የገዢው ፓርቲ አባል ናቸው፡፡ ምንመ እንኳን ፌዴሬሽኑ ከፖለቲካ ገለልተኛ አካል በመሆን መስራት ሲገባው አሁን ባለው ሁኔታ ግን ይህ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ ማናቸውንም ጥያቄዎችን ማንሳትም ሆነ ወደ በላይ አካል ማቅረብ በራሱ ከባድ ነው፡፡ አንደኛ ሁሉም የተሳሰሩ ስለሆኑ ምላሽ አታገኝም፤ ድምፄን አሰማለሁ ያልክም እንደሆነ የፖለቲካ ታፔላ ተለጥፎብክ ሌላ ችግር ይደርስብካል፡፡
ኢ.ዛ.፡- አንተ እንደ አንድ አትሌት ለዚህ መፍትሄው ምንድነው ትላለክ?
አትሌት ከላሊ፡- በርግጥ እኔ ፖለቲካኛ ስላልሆንኩና ብዙ ፖለቲካ ስላማላውቅ እንዲህ ነው ብዬ ስፊ ትንተና ልሰጥህ አልችልም፡፡ ግን እርግጠኛ ሆኜ የምነግርክ መንግስት ከአትሌቲክሱ ውስጥ ጣልቃገብነት ማቆም አለበት፡፡ አጠቃላይ የስርዓት ለውጥ ካልመጣ በፌዴሬሽኑ አካባቢ ብቻውን ለውጥ ይመጣል ወይ የሚለው ነግር ለመመለስ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን በአትሌቲክስም ይሁን በሌላው የህይወት መስክ ወጣቱም፤ የሚቀጥለው ትውልድም ይኼን ስርዓት በርትቶ መታገል አለበት ነው የምለው፡፡ ሌላ ምንም አማራጭ የለኝም፡፡
ኢ.ዛ.፡- በመጨረሻ እንደው ሌላ የምትጨምረው ወይም የምታስተላልፈው መልዕክት ካለህ?
አትሌት ከላሊ፡- በይበልጥ ወጣቱ የተወሰደበትን የእኩልነት እና የነፃነት መብቱን፣ ለእውነት እና ለማንነቱ መታገል አለበት፡፡ ሰው በድህነቱ በብሔሩ ወይም በፖለቲካ አስተሳሰቡ ሲጨፈጨፍ ዝም ብሎ መመልከት ሳይሆን አንድ ሆኖ መታገል አለበት፡፡ ሁሉም በሚችለው አቅሙ ማለት ነው፡፡
ኢ.ዛ.፡- ስለሰጠሀን ቃለምልልስ እናመሰግናለን፡፡
አትሌት ከላሊ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

Source: ecadforum.com

No comments:

Post a Comment