Wednesday, November 4, 2015

በድርቅ በተጠቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች የውኃ ወለድ በሽታዎች ሥጋት ተፈጠረ


UN: 9 million need aid in drought-hit East Africa
(ሪፖርተር ጋዜጣ) በአማራ ክልላዊ መንግሥት በድርቅ በተጠቁ በተለያዩ ዞኖች የተከለሉ ውኃ ምንጮች ውስንነት፣ ከንፅህና ጋር ለተያያዙ በሽታዎች መፈጠር ምክንያት መሆኑ ተገለጸ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በዚህ ሳምንት በወጣው ሪፖርት፣ ‹‹ስካቢስ›› የተሰኘ ወረርሽኝ በምሥራቅ ጎጃም፣ በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ወሎና በዋግ ህምራ ዞኖች በሚገኙ 20 ወረዳዎች መከሰቱን አስታውቋል፡፡ በዋግ ህምራ ዞን ብቻ 88,905 ግለሰቦች በወረርሽኙ መያዛቸው ታውቋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበሽታው ለተጠቁ ሥፍራዎች መድኃኒቶችን በመላክ ላይ መሆኑን የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ የችግሩ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ የተለያዩ ዘርፎችን ትብብር የሚጠይቅ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

በሽታው ተዛማች በመሆኑ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተጀመረው ጥረት በአፋጣኝ ተስፋፍቶ መቀጠል እንደሚኖርበት የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ወረርሽኙ የተከሰተው ከድርቁ ጋር ተያይዞ እንደሆነ በሪፖርቱ አስፍሯል፡፡

ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የምግብ ፕሮግራም የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ቁጥር ከሌላው ጊዜ በ20 በመቶ መጨመሩን፣ የተጎጂዎቹ ቁጥር በየወሩ እየጨመረ መሄዱን ጽሕፈት ቤቱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በመስከረም ወር የተመዘገቡ በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር 35,216 የነበረ ሲሆን፣ በነሐሴ ወር ከተመዘገቡት 43,391 ሕፃናት የ19 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በመስከረም ወር የተመዘገበው በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ቁጥር ከሌላው ማንኛውም ዓመት የ20 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በአማራ ክልል እንደሆነ የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ በየወሩ በክልሉ 6,489 በምግብ ዕጦት የተጎዱ ሕፃናት ወደ ምግብ ፕሮግራም እንደሚገቡ ጠቁሟል፡፡

በኤልኒኖ ምክንያት በተፈጠረው አየር መዛባት የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ መምጣቱን ጠቅሶ፣ እየጨመረ የመጣውን የምግብ ዕርዳታ ፍላጎት መጠን ለማሟላት የኢትዮጵያ መንግሥት ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርብም አጥጋቢ ምላሽ አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. የ2015 እና የ2016 የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል የገንዘብ ምንጭ አለመኖሩ አሳሳቢ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ እ.ኤ.አ. ለ2016 የሚያስፈልገው ዕርዳታ በአስቸኳይ መገኘት እንዳለበት የገለጸው ጽሕፈት ቤቱ፣ ዕርዳታውን አጓጉዞ ከሚፈለገው ሥፍራ ለማድረስ ከሦስት እስከ አምስት ወራት ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚኖርበት ጠቁሟል፡፡

መንግሥት ከለጋሾች የሚፈለገውን ያህል የገንዘብ ድጋፍ ባለማግኘቱ ሁኔታዎች በከፉበት አካባቢ በራሱ ወጪ ዕለታዊ ዕርዳታዎች በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ከመንግሥት የመጠባበቂያ ምግብ ክምችት 50,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴና 300 ሜትሪክ ቶን የምግብ ዘይት በመከፋፈል ላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የከብቶች መኖ በመታደል ላይ መሆኑን፣ የውኃ ጉድጓዶች ጥገና ሥራ እየተከናወነ እንደሆነና የውኃ ማጣሪያ ኬሚካሎች በመሠራጨት ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ድርቅ ምክንያት 8.2 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የዕርዳታ አቅርቦቱ ካልተፋጠነና የአየር ፀባዩ ካልተለወጠ የተረጂዎች ቁጥር በሁለት ወራት ውስጥ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ተገምቷል፡፡

The post በድርቅ በተጠቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች የውኃ ወለድ በሽታዎች ሥጋት ተፈጠረ appeared first on Zehabesha Amharic.

Source:: Zehabesha

No comments:

Post a Comment