Tuesday, November 24, 2015

ዜጎች እርዳታ እንዲደረግላቸው እየጠየቁ ቢሆንም እስካሁን በቂ ምላሽ ሊሰጣቸው አልቻለም


ኀዳር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከተለያዩ ክልሎች ለኢሳት የሚላኩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እርዳታ የሚጠይቁ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ በቂ የሆነ እርዳታ እየተከፋፈለ አይደለም።
በአማራ፣ በትግራይ ፣ በሶማሊ፣ በደቡብና በአፋር የእለት ደራሽ ምግብ የሚጠይቁ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ህጻናት በአልሚ ምግብ እጥረት የተነሳ ለበሽታ እየተዳረጉ በመሞት ላይ ናቸው፡፡የረሃቡ ሁኔታ አስከፊ እየሆነ ቢመጣም በመንግስት ባለስልጣናት በኩል የሚሰጠው መግለጫ እርስ በርስ የሚጣረስ በመሆኑ፣ በተረጅዎች ህይወት ላይ ተጽኖ እያሳረፈ ነው።
በአማራ ክልል 69 ወረዳዎች በድርቅ የተጠቁ ሲሆን፣ ባለፈው መስከረም ወር በተደረገ ጥናት 1 ሚሊዮን 400 ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚሹ ቢገልጽም፣ ይህ አሀዝ በመጪው ወር ይፋ በሚደረው ጥናት ላይ በእጥፍ ጨምሮ እንደሚገለጽ መረጃዎች ያመለክታሉ። የክልል አደጋ መከላከል ዝግጁነት ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ሽለስ ተመስገን በአንዳንድ አካባቢዎች በክረምቱ ወራት ለ2 ቀን ብቻ ዝናብ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ወትሮ ዝናብ እጥረት አጋጥሟቸው የማያውቁት ወረዳዎች እንኳ የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸው መሆኑን ባለስልጣኑ አልሸሸጉም። የዋግ ህምራ ሁሉም ወረዳዎች ፤ የሰሜን ጎንደር ምስራቃዊ ክፍል- በለሳ ፣ ጠለምት ፣ወገራ ፣ ጃን አሞራ ፣ የደቡብ ወሎ ሁሉም ወረዳዎች- መቅደላ ፣ አርጎባ ፣ ከላላ ፣ ከዚህ በፊት ተርበው የማያውቁት የምስራቅ ጎጃም የአባይ አዋሳኝ ስምንት ወረዳዎች በአጠቃላይ 800 ቀበሌዎች በርሃብ ውስጥ እንደሆኑ የክልሉ የአደጋ መከላከል ጽ/ቤት ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡
በዋግ ህምራ ስሃላ ወረዳ በአመት ውስጥ ሁለት ቀናት ብቻ ነው ዝናብ ያገኘው። ሰቆጣ ፤ አበርገሌ ፤ ደሃና በከፋ ሁኔታ በድርቅ ተጠቅተዋል። በሰሜን ወሎ፣ የራያ ሰፊ መሬት ዝናብ ካዬ በመክረሙ ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖበታል። በክልሉ በድርቅ ከተጎዱት 69 ወረዳዎች መካካል 35 ቱ በከፋ ሁኔታ ላይ ሲገኙ 34ቱ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ተጠቅተዋል። በሁለተኛ ደረጃ ተጠቂ የተባሉት ለሶስት ወራት የሚያቆይ የእህል ክምችት ያላቸው ናቸው፡፡
በአሁኑ ስዓት መንግስት ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ ወይም በቆሎ ለወር ደግሞ ግማሽ ሌትር ዘይት እያደለ መሆኑን ባለስልጣኑ ተናግረዋል።
በአሁኑ ስዓት ቀዳሚው ችግር የመጠጥ ውሃ እጥረት ነው ያሉት ኃላፊው፣ በምግብ እና የጤና ችግርም በውሃ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ የንፅህና እና የውሃ ወለድ በሽታዎች ተከስተዋል ብለዋል፡፡
በአልሚ ምግብ እጥረት የተጎዱ እናቶች እና ህፃናት አሉ ያሉት ባለስልጣኑ ፣ ህፃናት በአልሚ ምግብ ችግር መሞታቸውንም ይፋ አድርገዋል በትግራይ ደግሞ ከ52 ወረዳዎች 36ቱ በድርቅ ተመተዋል። በክልሉ የሚሰጠው እርዳታ ከፖለቲካ ጋር መያያዙንም ተረጅዎች እየገለጹ ነው። የመንግስት እዳ እና የወይን ጋዜጣ ያልከፈሉ ሰዎች እርዳታ እንደማያገኙ እንደተገለጸላቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በሰሜን ጎንደር በዳባት ወረዳ ቦሲያ፣ አጋምዜና ሌሎችም ቀበሌዎች የተረጅውን ቁጥር ለማጥናት ለተላኩ ባለስልጣናት በሚል እያንዳንዱ ተረጅ በነፍስ ወከፍ 10 ብር እንዲያዋጣ ተገዶ፣ አጥኚዎች በግና ፍየል ታርዶላቸው ሲመገቡ መሰንበታቸውና ተረጅዎች ” ብዙዎቻችንን ሳይመዘግቡን ሄዱ” በሚል መበሳጨታቸውን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአካባቢው ሰው ለኢሳት ገልጸዋል። ጥናቱን ለማካሄድ የተላኩት ከግብርና አቶ አስችሌ አሰፋ፣ ከከምግብ ዋስትና ወ/ሮ አስካለማርያም ተገኘ ፣ ከብአዴን የድርጅት ጉዳይ አቶ ሰጠኝ ንጉሴ እና ሁለት ሌሎች ተወካዮች ናቸው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሳምንታዊ ዘገባ ባወጣው መረጃ ደግሞ ድርቁ ከፈጠረው ቻና በተጨማሪ፣ 210 ሺ 600 ሰዎች በጎርፍ አደጋ ሊፈናቀሉ ይችላሉ ብሎአል።መንግስት የእርዳታ እህል በቅርቡ ስራ የጀመረውን ባቡር በመጠቀም ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ ለማመላለስ ማቀዱን ገልጿል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment