Monday, October 19, 2015

የአለም የመገናኛ ብዙሃን ስለኢትዮጵያ ድርቅ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ላይ ናቸው


ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከታላላቆቹ የአለም የመገናኛ ብዙሃን መካከል ዘ ኒውዮርክ ታይምስና ቢቢሲን ጨምሮ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ድርቅ የዜና ሽፋን በመስጠት ላይ ሲሆን፣ ዘ ኒዮርክ ታይምስ ባወጣው ዘገባ ድርቁ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።
“ያሲን ሙሃመድ ከአነስተኛ የእርሻ ማሳው ላይ እየወሰደ ጫት ይቅማል፣ ለምን ተብሎ ሲጠየቅ ፣ ጫት ረሃብን ያስታግሳል “የሚል መልስ መስጠቱን የዘገበው ዘ ኒዮርክ ታይምስ፣ በመኢሶ አካባቢ ለወትሮው በክረምት ወር ይዘንብ የነበረውን ዝናብ ዘንድሮ አንድ ጊዜ ብቻ መዝነቡን ገልጿል።
ይህ ኢትዮጵያ በ10 አመታት ውስጥ የገጠማት ከባዱ ድርቅ ነው ያለው ጋዜጣው፣ ነዋሪዎች መሰደድ መጀመራቸውን ይገልጻል። የ50 አመቱ ጎልማሳ አቶ ያሲን፣ በሰአት ምግብ መመገቡን ማቆሙን ገልጾ፣ እስከ ሚቀጥለው የመኸር ወቅት ከብቶቹን ቢሸጥ እንኳን ቤተሰቡን ለማቆየት እንደማይችል ገልጿል።
“ሌሎች አርሶ አደሮች አካባቢውን ለቀው ” መሄዳቸውንም አቶ ያሲን አክለዋል። መንግስት 8 ሚሊዮን 200 ሺ ህዝብ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ቢገልጽም፣ አሃዙ እስከ 16 ሚሊዮን እንደሚደርስ ጋዜጣው የተመድን መረጃ ዋቢ በማድረግ ጠቅሷል።
መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ድህነት ለመቀነስ እና መንገዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን እንዲሁም የጤና ተቋማትን ቢገነባም፣ የሰዎችን ነጻነት እና የብዙሃን ፓርቲ ዲሞክራሲን ለመገንባት አለመቻሉን ገልጾ፣ ባለፈው ምርጫ 547 የፓርላማ መቀመጫዎችን በሙሉ መውሰዱን ዘግቧል። መንግስት ድርቁን ለመሸፋፈን ሙከራ ማድረጉን ተችዎች እንደሚገልጹ የዘገበው ዘ ኒውዮርክ ታይምስ፣ ይሁን እንጅ የአደጋ መከላከልና ዝግጅኑት ሃላፊ ምትኩ ካሳ መንግስት 192 ሚሊዮን ዶላር በማዘጋጀት ፈጣን ምላሽ መስጠቱን በመግለጽ ትችቱን ተከላክለዋል።
አቶ ምትኩ ጥረቱ በቂ ባለመሆኑ ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፍልግ ተናግረዋል። አሁን የታየው ችግር አመቱን ሙሉ እንደሚቀጥልና እስከ 15 ሚሊዮን ህዝብ እንደሚራብ ጋዜጣው ጠቅሷል።
በተለይ አሚባራ በሚባለው የአፋር አካባቢ በርካታ እንስሳት ማለቃቸውን የጠቀሰው ጋዜጣው፣ ሁመድ ካሚል የተባሉ የ42 አመት ጎልማሳ 30 የሚሆኑ ላሞቹ በርሃብ እንደሞቱ ገልጿል። አቶ ሃሚድ 7 ልጆቻቸውን ለማብላት ቀሪ ላሞቻቸውን ለመሸጥ እየተገደዱ መሆኑንም ገልጸዋል። መንግስት ምንም ድጋፍ እየሰጣቸው አለመሆኑንም አቶ ሃሚድ ለጋዜጣው ሪፖርተር ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በጥቅምት ወር ውስጥ በትግራይ፣ አዊ፣ ባህርዳር ዙሪያ፣ ምእራብ እና መስራቅ ጎጃም፣ ሰሞንና ደቡብ ጎንደር፣ ዋግ ህምራ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ኦሮምያ ዞን፣ በአፋር ደግሞ ዞን 3 እና 5 ፣ አብዛኛው የቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢና ጋምቤላ፣ ኢሉባቡር፣ ጅማ፣ ምስራቅና ምእራብ ወለጋ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ሆሮ ጉድሩ፣ አርሲ፣ ባሊ፣ ምስራቅና ምእራብ ሃረርጌ፣ ከፋ እና ቤንች ማጂ ዞን፣ ሲቲ፣ ጂጂጋ ፣ ፊቅ፣ ደጋሃቡር፣ ሊቢን፣ አፍዴር፣ ጎዴ፣ ኮራሄ እና ዋርዴር ዞን እንዲሁም ሃረሪ፣ ድሬዳዋን አዲስ አበባ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ከመቻሉ በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎች ሊበላሹ ይችላል ሲል ብሄራዊ የጎርፍ መከላከያ ተቋም አስታውቋል።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment