ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሩዋንዳ፡ ኪጋሊ በተደረገው የአቶ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ ስብሰባ ላይ በህገመንግስት ላይ የመግባባትንና የብዝሃነትን አስፈላጊነት አመልክተዋል። *
በተጨማሪም መንግስት ለሁለተኛ ዙር የእድገትና ለውጥ/ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (GTP II) ለመንደፍ ካደራጃቸው ኮሚቴዎች የአንዱ ኮሚቴ አላማ “ዴሞክራሲን ማስፈን፣ ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራን የተመለከተ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ስምንት አባላት አሉት፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የአምስት ዓመት ዕቅድ የሚነድፈውን ኮሚቴ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ይመሩታል፡፡ ” **
የብሔራዊ መግባባትን አስፈላጊነት በሚመለከት ከገዢው ፓርቲ አስቀድሞ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በድርጅት መርሃ ግብራቸው ላይ ጭምር አቋም የወሰዱ ህጋዊ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና እንዲሁም ከአገር ውጪ የተደራጁ በሰላማዊ ትግል መታገል የመረጡ ድርጅቶች ናቸው። የትጥቅ ትግል ከመረጡትም ውስጥ የሂደታዊና ጥገናዊ ለውጥ (reform) ደጋፊዎች በመኖራቸውና፥ ብሔራዊ መግባባት የሂደታዊና ጥገናዊ ለውጥ ዋና አካል በመሆኑ፥ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ በሚታገሉ አካላት ጋር ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነቱ የታመነበት ነው ማለት ይቻላል።
ብሔራዊ መግባባት በጥልቀት ሳይሆን ላይ ላዩን፥ አልፎ አልፎ ሲዳሰስ ቆይቷል። በተጨማሪም ከብሔራዊ መግባባት ጋር በሚያያዘው በብሔራዊ እርቅ፥ ወቅታዊና ታሪካዊ ቁስሎችን ለፓለቲካ ፍጆታ ከማዋል ባለፈና ዘለቄታዊ በሆነ መልኩ፥ ቅራኔዎችን ለመፍታት እውቅናና ትኩረት አልተሰጠም። አለመግባባት የአገራችን ፖለቲካ ቅራኔ ምልክትና መገለጫ ነው። አለመግባባት መኖሩን የሚክድ ድምፅ ከገዢው ፖርቲም ሆነ ከተቃዋሚዎች ጎልቶ ባይሰማም፥ ወደ መግባባት እንዴት እንደምንደርስ ግን በዝርዝር የቀረቡ መሰረታዊ ነጥቦች የሉም።
በ65Percent.org ሳምንታዊ የውይይት መድረክ (ፎረም 65) ላይ ካነሳናቸው ጉዳዮች አንዱ በብሔራዊ መግባባት ላይ ለመሳተፍ መሰረታዊ መስፈርቶችን መለየት ነው። ሶስት መሰረታዊ ብለን ያነሳናቸው ነጥቦች በዚህ ፅሁፍ ቀርበዋል። ***
በብሔራዊ መግባባት ላይ ሊሳተፉ ሚችሉ ምን አይነት መስፈርት ሚያሟሉ እንደሆኑ ለይቶ ማወቁ የመግባባት ሂደት ለመጀመር ቀዳሚ ጉዳይ ነው። ለብሔራዊ መግባባት ስለኢሕአዴግ፥ ስለብሔረሰቦችና ስለታሪክ የጋራና ተመሳሳይ አቋም የያዙ ግለሰቦች፥ ስብስቦች፥ ቡድኖች፥ ድርጅቶችና ፓርቲዎች “በምን ላይ እንግባባ?” ሚለው ጥያቄ ላይ አብረው ለመወያየት የሚያስችል መሰረት ሊኖራቸው ይችላል።
ሶስቱ ነጥቦች፦
1. ስለኢሕአዴግ
************
ገዢው ፓርቲ አገሪቱን እስከገዛ ድረስ የብሔራዊ መግባባት ሂደት አካል ነው። ኢሕአዴግን እንደ ጠላት ሚፈርጁ አካላት በብሔራዊ መግባባት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ አቋማቸው ለገዢው ፓርቲ ህልውና ዋስትና ስለማይሰጥ፥ ኢህአዴግን እንደ ጠላት መፈረጃቸውን ትተው ኢሕአዴግን እንደ ተፎካካሪ ቢመድቡት በብሔራዊ መግባባት ሂደት ውስጥ ጠቃሚ ተሳትፎ ማድረግ ይችላሉ ብለን እናምናለን ።
የአገሪቱ የሃይል ሚዛን እስካልተለወጠና ኢሕአዴግ የበላይነቱን ጨብጦ እስከቀጠለ ድረስ ለኢሕአዴግ ህልውና ዋስትና የሚሰጡ፥ ህገመንግስቱን ሚቀበሉና በሂደት ማሻሻል እንደሚቻል የሚያምኑ አካላት በብሔራዊ መግባባት ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ መሰረታዊ መስፈርት እንደሚያሟሉ እንረዳለን።
2. ስለብሔረሰቦች
*************
ኢትዮጵያ የብሔሮች አገር ናት። ይሄንን ጭብጥ ሚክዱ፥ ሚያጣጥሉና የብሔሮችን ህልውና “ጎሳ”፥ “ጎጥ” በማለት እውቅና ሚነሱ አካላት በአገር ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተቀብለው ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ ገንቢ ሚና መጫወት ይችላሉ።
‘የግለሰብ መብት ከተከበረ የብሔረሰቦች መብትም ይከበራል’ የሚለውን አቋም ሚያስተናግዱ አካላት የብሔረሰቦችን መብት እንደ አበይት (primary) ሳይሆን እንደ ንዑስ (secondary) ጉዳይ ያስቀምጡታል።
የግለሰብና የቡድን መብቶች ሊነጣጠሉ አይችሉም፥ ተመጋጋቢ ናቸው። የዜጎች ግላዊ መብት እንዲከበር የቡድን መብታቸውም መከበር ይኖርበታል፥ የቡድን መብታቸው እንዲከበር ግላዊ መብታቸውም መከበር ይኖርበታል።
በብሔረሰቦች ጉዳይ ላይ የሚወሰዱ አቋሞች በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ዓመታት የሰረፀውንና የማይቀለበሰውን የብሔር ተኮር ማንነት ግንባታ (empowerment) ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ፥ የግለሰብንና የብሔሮችን መብቶች እኩል ዋጋ ሰጥቶ በብሔራዊ መግባባት ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ አቋሞችን ማሻሻል ይቻላል።
3. ስለታሪክ
*********
የዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ዛሬ ባለንበት የፓለቲካ አለመግባባት ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ መኖሩ አያከራክርም። የመዘናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ሁሉም መጥፎ እንዳልሆነ ሁሉ፥ ሁሉም መልካም ሊሆንም አይችልም።
ታሪካዊ ጥቁር ነጥቦችን እንደ አገር በአንድነት እውቅና ሰጥተን ወደፊት መራመድ ለብሔራዊ መግባባት ገንቢ እርምጃ ነው። ስለሆነም ታሪክን በሚመለከት ቢያንስ በመርህ ደረጃ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ በደሎች እንደነበሩ መቀበል በብሔራዊ መግባባት ለመሳተፍ ወሳኝ መስፈርት መሆኑን እንረዳለን።
በአገራችን ብሔራዊ መግባባት ላይ እንድንደርስ ገንቢ ውይይት ማድረግ ዋንኛው መንገድ ነው። ከላይ በተጠቀሱት ነጥቦች ላይ ገንቢ ሃሳቦችን እናስተናግዳለን።
መግባባትን እናውርስ!
65Percent.org
info@65Percent.org
www.Facebook.com/65PercentOrg
———
* “We need to have a plural society [where] both parties, media and organized groups all have their say in the decision making bringing the country forward. Have a broad consensus on basic issues, specially on constitution.” https://youtu.be/JnGWCm208og Accessed on Oct 25, 2015; Go to video time 1:12:00
** http://www.ethiopianreporter.com/index.php/news/item/8580, Accessed on Oct 25, 2015
*** “ፎረም 65” በብሔራዊ እርቅና መግባባት ላይ ሳምንታዊ ዝግ ውይይት የሚያደርግ የ65Percent.org መድረክ ነው።
The post ፎረም 65፦ በብሔራዊ መግባባት ለመሳተፍ መሰረታዊ መስፈቶች ምን ይሁኑ? appeared first on Zehabesha Amharic.
Source:: Zehabesha
No comments:
Post a Comment