Monday, September 28, 2015

ቤት ሰሪ የመንግሰት ሰራተኞች አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን ገለጹ


መስከረም ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በባህርዳር ከተማ የ1997ቱን ምርጫ ውጤት ተከትሎ በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ገብቶ የነበረው ኢህአዴግ የህዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በሚል የቤት ፈላጊዎችን በማህበር ካደራጀ በሗላ ፣ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ እንዲቆጥቡ በማድረግ ከ9 ዓመታት በሗላ የቤት መስሪያ ቦታቸውን ለቤት ሰሪዎች ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጅ ቤቱን መስራት የሚችሉት መንግስት ባወጣላቸው የቤት እቅድ መሰረት ባለፎቅ ቤት ብቻ መሆኑ ቤት ሰሪዎችን ድንጋጤ ላይ ጥሎአቸዋል። የቤቱን መሰረቱን ካላወጣችሁ የቆጠባችሁት 80ሺ ብር አይመለስላችሁም በመባላቸው ፣ እነዚህ ከ90 በመቶ በላይ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት የቤት ፈላጊዎች የቤቱን መሰረት ለማውጣት የሚያስችል ገንዘብ እንደሌላቸውና የሚኖሩበት የኪራይ ቤት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየጨመረ መምጣቱን በመግለፅ ለዘጠኝ ዓመታት የቆጠቡት ገንዘብ እንዲመለስላቸው በምሬት ቢጠይቁም ምላሽ አላገኙም፡፡
አንዳንድ በጣት የሚቆጠሩ የማህበር አባላት ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ስላላቸው መሰረቱን ማውጣት የቻሉ ሲሆን አብዛኞቹ ደግሞ ቦታውን ለመሸጥና ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ሁኔታው እያስገደዳቸው ነው፡፡ በዚህ አዲስ የመኖሪያ መንደር መንገድ ፣ ውሃና መብራት መንግስት ሊያስገባላቸው እንዳልቻለ ግንባታውን የጀመሩ አባላት ይናገራሉ፡፡
ከፍተኛው የመንግስት ደሞዝ ጣሪያ ከ5000 ብር በማይበልጥበትና የኑሮ ውድነቱ እጅግ በናረበት ሁኔታ ቤተሰብ መስርቶ በኪራይ ቤት ለሚኖር ሰው መንግስት በሰጠው የቤት ፕላን መሰረት ብቻ ቤት እንዲሰሩ መደረጉ ከስህተትም የከፋ ነው ሲሉ ሰራተኞች ይገልጻሉ። በሌላ ዜና ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቦሎቄ እንዲያመርቱ ምክርና ድጋፍ የተደረገላቸው አርሶ አደሮች ምርቱን የሚሸጡበት
የገበያ ሁኔታ እንዳልተመቻቸላቸውና ምርቱ ሲደርስ መንግስት ችላ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ የገበያው ሁኔታ ያስጨነቃቸው በሌሎች አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የሌሎች የምግብ ሰብሎች ዋጋ ይጨምራል ብለው በመስጋታቸው ነው፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ፣ ” የ ቦሎቄ ዋጋ መውረዱን ተከትሎ የሌሎች መሰረታዊ የምግብ
ፍጆታና ቁሳቁሶች ወጪ በሚሸፍን ዋጋ መሸጥ ካልቻሉ ” አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ይናገራሉ። መንግስት ለውጭ ገበያ በማሰብ ብቻ አርሶ አደሮች ቦሎቄ እንዲያመርቱ ካደረገ በሗላ፣ ሌሎች የገበያ አማራጮችን ባለማመቻቸቱ በውጭ የገበያ ዋጋ ብቻ ተወስነው እንዲሸጡ እየተገደዱ መሆኑን አክለው ይገልጻሉ።

Source:: Ethsat

No comments:

Post a Comment